"የቆየ ወዳጅነት" የተባለውን የሩስያ-ቻይና ግንኙነት ምዕራባውያን እንዴት ተመለከቱት? የምሥራቃውያንስ ምስጢር ምንድነው?

1 Mon Ago
"የቆየ ወዳጅነት" የተባለውን የሩስያ-ቻይና ግንኙነት ምዕራባውያን እንዴት ተመለከቱት? የምሥራቃውያንስ ምስጢር ምንድነው?

የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተደጋጋሚ የሚመላለሱባትን እና "የጥንት ወዳጅ" ያሏትን ቻይናን ጎብኝተዋል። ቻይናም ለክብሯም ለእንግዳዋም ክብር በወታደራዊ ትርዒት የታጀበ የቀይ ምንጣፍ አቀባበል አድርጋላቸዋለች።

በሀገራቸው ያለተቀናቃኝ ምርጫ አድርገው፣ በትረ ሥልጣናቸውን አደላድለው፣ ካቢኔያቸውንም በመሰረቱ ማግስት ወደ ቻይና የማቅናታቸው ጉዳይ በየዋህነት ብቻ የሚታይ አልሆነም። አንድምታው ብዙ ነው የሚሉት ምዕራባውያን ይህ ጉዳይ የኃይል ሚዛኑን ወደ ምሥራቅ ለማዘንበል የሚቀመር የምስራቃውያን ምስጢር መሆኑን የተረዱ መስለዋል።

በእርግጥ በየሚዲያዎቻቸው የፑቲንን ጉብኝት ባላየ ለማለፍ ቢፈልጉም፤ አንድምታው ከፍ ያለ በመሆኑ በፍላጎቶቻቸው ልክ በጥቂቱ ዘግበውታል።

የሩቅ ምሥራቋ ቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግን ይዛ የአሜሪካ ፊታውራሪነትን አንዳንዴ እየቀማች፣ አልፎ አልፎ አብረን ካልተጓዝን እያለች፣ መገዳደር ከያዘች ሁለት አስርት ዓመታት አልፈዋል። የዓለም መሪነት ከእጃችን አይወጣም ዓይነት ትግል ውስጥ የገቡት ምዕራባውያኑም የቻይናን ግስጋሴ በዓይነ ቁራኛ እየተከታተሉ እየወደቁም፣ እየተነሱም የተሳካላቸው አይመስሉም። በየትኛውም ሀገር ውስጥ የአሜሪካን ጥቅም እናስከብራለን በሚል ወታደር አሰማርታ መንግሥት ማውረድ እና ማንገሥ የምትችለው ሀገር እና ወዳጆቿ በሴራ ፖለቲካ ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ የሚጓዝ አንድም ሀገር ከፊቷ እንዳይቆም አድርጋለች። በዚህ መንገድም ቢሆን ፊት ለፊት የማትጋፈጠው ቻይና ግን በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባቷ እና የትኛውንም ሀገር ጠላት እና ወዳጅ ብላ አለመፈረጇ የፖለቲካ ሴራን እንደ ሕልውናዋ ማስጠበቂያ ለምትጠቀመው አሜሪካ የሚስማማ አልሆነም።

ፊት ለፊት የማይገኘው እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን የማይፈቅደው የቻይና ፖሊሲ በአፍሪካ ውስጥ እየያዘችው ያለው ቦታ ቀላል የሚባል እንዳይሆን አድርጎላታል። በተለየ አቀራረብ አፍሪካውያንን ወዳጅ ለማድረግ የተነሳችው ቻይና በተለይም በመሰረተ ልማት ግንባታ ያላትን ቦታ ምዕራባውያን በቀላሉ የሚተኩት እየሆነ አይደለም።

በሌላ በኩል ምዕራባውያን ለወትሮው ፈጣሪውም ተጠቃሚውም እኛ ነን ይሉበት በነበረው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ቻይና እያመጣችው ያለውን ለውጥም በቀላሉ ሊገዳደሩት የሚችሉት ሳይሆን ለመከተል የሚገደዱበት እየሆነ ነው። ቻይና በአይሲቲ ዘርፍ እየገሰገሰችበት ያለው ፍጥነት እና በኤሌክትሪክ መኪና ዘርፍ ወደ ቀዳሚ ተመራጭነት እየመጣች መሆኗ ለዚህ ማሳያ ነው። ከምድር ውጭ ጨረቃ እና ማርስ ላይ በሚደረጉ ጥልቅ የህዋ ምርምሮች እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያሳየችው እመርታም ሌላ ዓለም የምትፈጥር አስመስሏታል።

የምዕራባውያን ማዕቀብ ተኮር ፖሊሲን የማትከተለው ቻይና ታዲያ በቀላሉ የማይበገር ኢኮኖሚ እና ወታደራዊ አቅም እየፈጠረች መሄዷ በቀጣይ የኃይል ሚዛኑን ወደ ምሥራቅ ልትወስደው እንደምትችል ለሁሉም ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል።

ይህን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋን እያሰፋች "የቆየ ወዳጅነት" የተባለውን የሩስያ ቻይና ትስስር በአግባቡ ማስኬዷ ደግሞ ተጨማሪ ተገዳዳሪ ኃይል እየያዘች ስለመሆኗ እያሳበቀባት ነው።

በዚህ በኩል ከአውሮፓ በዛ በኩል ደግሞ ከእስያ ጎረቤት የሆነችው ሩስያ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ ከምዕራባውያን ጋር እንደተፋጠጠች ነው። ሶቪየት ሕብረት ዳግም እንዳታንሰራራ ብሎም ተፈረካክሳ ከአንድ ህብረትነት ወደ ብዙ ሀገርነት ተገነጣጥላ በሩስያ ብቻ የተወሰነው የሶቪየት ስሜት እንደዛሬው ጠንካራ ሀገር ትሆናለች ተብሎ በማይገመት ደረጃ ለማፍረስ ምዕራባውያን ተሳክቶላቸዋል። ሩስያ ወደ ቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ዓይነት ኃያልነቷ ለመመለስም በቭላድሚር ፑቲን መሪነት ከ20 ዓመታት በላይ አንገቷን ደፍታ ሰርታለች። ምዕራባውያኑም ቢሆኑ ሶቪየት ህብረትን የማፈራረስ ጉዳይ በኩራት የሚናገሩት የአባቶቻችው ታሪክ አካል ነው። ይህም ሆኖ ለምዕራባውያኑ ራስ ምታት የሆነው ጉዳይ የሩስያ ኒውክሊየር መታጠቅ በመሆኑ ለዚህም ሌላ መፍትሄ ያሉትን መንገድ ተከትለዋል። አጥሯ ስር ከስምምነታቸው ውጭ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅትን (ኔቶን) አቋቋሙ። ፍጥጫው አደባባይ ወጥቶም ምዕራባውያን ዩክሬንን ወርራለች በማለት ሩስያን ለማሸነፍ እየሠሩ እንደሆነ ለዩክሬን በገፍ በሚያቀርቡት የጦር መሣሪያ ድጋፍ አረጋግጠዋል። ሩስያ በዚህ ውጥረት ላይ እያለች በፅኑ አቋም ከጎኗ የቆመችው ቻይና ነች። ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ተመሳሳይ አቋም እና መንበረ ምዕራባውያንን በመንበረ ምሥራቃውያን የመተካት ጽኑ ፍላጎት፣ በጋራ መሥራታቸው ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጓል።

ለዚህም ነው የሁለቱ ሀገራት የጋራ አቋም ለዓለም ሥርዓት አስጊ እንደሆነ ምዕራባውያኑ በየሚዲያዎቻቸው እየተነተኑ ያሉት። የፑቲን የቻይና ጉብኝት ሩስያ በካርኪቭ አቅጣጫ ባለው የጦር ግንባር እስከ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገብታ እያጠቃች ባለችበት ወቅት መሆኑ እና ዩክሬን ይህን ጥቃት ለመከላከል ከአሜሪካ የተላኩላት የጦር መሣሪያዎች እንደዘገዩባት ቅሬታ በምታቀርብበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ምዕራባውያን ሚዲያዎች ሌላ የትችት ሰበብ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። "አምባገነኖች" ብለው የሚጠሩአቸው መሪዎች መገናኘታቸው ያልጣማቸው ሚዲያዎቹ ታዲያ ይህ ግንኙነታቸው ቀጣይ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑን ለማሳየት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። አምባገነኖቹ ለምዕራባውያኑ "ዴሞክራሲ" ጠንቅ እንደሚሆኑም "ተንታኞችን" አቅርበው አስተንትነውታል።

እንደ አልጀዚራ ሀተታ በጉብኝቱ ወቅት መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂያዊ ትብብር ለማጠናከር የተፈራረሙ ሲሆን፤ ይህ ግንኙነታቸውም ሁከት በበዛበት ዓለም ውስጥ የመረጋጋት ኃይል ይሆናል ተብሏል።  

ሺ ጂንፒንግ ይህ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ስምምነት የትኛውም ሦስተኛ ሀገር ጥቅም ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ብቻ ለማጠናከር እንዳለመ ጠቅሰው፣ የዩክሬን ግጭትም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ፍላጎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ሺ የሩስያ እና ቻይና ግንኙነት በዓለም ላይ እየሰፈነ ያለውን የአንድ ቡድን የበላይነት ለማስቀረት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት መናገራቸው ለምዕራባውያኑ መራር እንዲሆንባቸው አድርጎታል።

የአልጀዚራዋ ዘጋቢም ታዲያ ፕሬዚዳንት ሺ "የአንድ ወገን የበላይነት" ሲሉ አሜሪካ ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ጥርጥር የለውም ስትል ጽፋለች።

ፑቲን ከወዳጃቸው ቻይና የዩክሬንን ግጭት በሰላም እንዲፈታ የቀረበውን ሀሳብ በበጎነት በማየት፣ ነገሩ በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል። ለዚህም ምክንያቱ አሉ ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ የሰላም ቁልፉ በራሷ በዩክሬን እና በምዕራባውያን አጋሮቿ እጅ በመሆኑ ሊሳካ እንደማይችል አስታውቀዋል።

የሩስያ-ዩክሬን ግጭትን በተመለከተ ቻይና የሩስያን ድርጊት አለማውገዟ ምዕራባውያንን አላስደሰተም። በስኮትላንድ የሴንት አንድሩስ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዛንግ ቺ፣ ቤጂንግ በሩስያ-ዩክሬን ግጭት ላይ ያላት አቋም ከምዕራባውያን መለየቱ በቻይና-አውሮፓ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ለሺንዋ በሰጡት ሃሳብ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ቡድን 20 ውስጥ ያለውን ሚዛናዊ ያልሆነ አካሄድ፣ እንዲሁም ቻይናን ትኩረት ያደረገውን የአውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ጥምረት የሚገዳደር ጠንካራ ህብረት ያስፈልገናል ባይ ናቸው።

ቻይና የውጭ ፖሊሲያቸው ቀዳሚ ትኩረት እንደሆነች አዲሱን የሥልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ የገለጹት ፑቲን፣ ይህን ግንኙነታቸውን "አብሮነታችንን የሚያጎለብት" በማለት አወድሰውታል። እናም አሁን ከኒውክሊየር እና ከኃይል ትብብር አንስቶ እስከ ምግብ አቅርቦት እንዲሁም የቻይና መኪና አምራቾችን ሩስያ ውስጥ እስከ ማቋቋም እንዲደርስ የመፈለጋቸው ነገር ቀድሞም ቢሆን የተጀማመረ ነገር እንዳለ አመላካች ሆኗል።

የሩስያን ጋዝ እና ነዳጅ አንጠቀምም ያለው የምዕራቡ ዓለም ጎራ ምንም እንኳ በኃይል እጥረት አረንቋ ውስጥ ቢገባም፤ በአንጻሩ እርምጃው ይጎዳታል የተባለችው ሩስያ ከቻይና እና ከህንድ ያገኘችው የገበያ ፍላጎት ዳግም ወደ ምዕራብ እንዳትዞር የሚያደርጋት ዕድል ነው ተብሎላታል።

ሁለቱ መሪዎች ባለፉት አሥርተ ዓመታት ከ40 ጊዜያት በላይ መገናኘታቸው የቆየ ወዳጅነታቸውን ማረጋገጫ እንደሆነ የምትጠቅሰው የአልጀዚራዋ ካትሪን፣ የሁለቱ የቆየ ወዳጅነት እንዲቀጥል የሚሹት ሺ ጂንፒንግ፣ “ቻይና ከሩስያ ጋር ጎረቤት፣ መልካም ወዳጅ እና ጠንካራ አጋር ሆና ለመቀጠል ዝግጁ ናት" ማለታቸውን ገልጻለች።

በሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የምርምር ተቋም ተባባሪ አባል የሆኑት ሳሪ አርሆ ሃቭረን፥ ሩስያ በአሜሪካ የሚመራውን የዓለም ሥርዓት በመቀየር ለሁለቱ የሚመች ለማድረግ የቻይና አጋርነት ቁልፍ ሚና አለው ይላሉ። ታይዋንን እንደ ቻይና ሉዓላዊ ግዛት የምትመለከተው ሩስያ በታይዋንም ሆነ በሌላ ምክንያት በኢንዶ ፓሲፊክ አካባቢ ቻይና ላይ የሚፈጠረውን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት ከቻይና ጎን መቆሟ አይቀሬ እንደሆነም ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ቻይናን ረፍት ለመንሳት ታይዋንን ለሚጠቀሙት ምዕራባውያን ተጨማሪ መጥፎ ዜና ነው።

ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ትስስሮቻቸውን አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ በጃፓን ባህር እና በምሥራቅ ቻይና ባህር ላይ የጋራ የጦር ልምምድ ማድረግን ጨምሮ አንዳቸው ወደ ሌላቸው ግዛት በነጻነት በመግባት የጦር ኃይል ሥልጠና ማደራጀታቸው ለዚህ የሩስያ ጠንካራ አቋም እንደ ማሳያ ይቀርባል። 

ይህ ወታደራዊ ትብብር አሜሪካ ውቅያኖስን ተሻግራ አውሮፓ ላይ ያቋቋመችውን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅትን (ኔቶን) መገዳደርን ከግምት ያስገባ እንደሆነም ነው የሚነገረው።

ከጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብራቸቸው ባሻገርም የደቡብ ደቡብ ትብብር አካል የሆነውን ብሪክስን የመሰረቱት ሁለቱ ሀገራት፣ አሁን ላለው የዓለም የኃይል አሰላለፍ ጠንካራ ተገዳዳሪ መሆናቸውን ነው ተንታኞች የሚገልጹት።

ብዙ በምዕራባውያን የማዕቀብ ጫና እና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የተማረሩ ሀገራት አሁን ባለው ቁመናው ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየታቸው ደግሞ እስካሁን የዓለምን 40 በመቶ ያክል የህዝብ ቁጥር የያዘውን የብሪክስ ግስጋሴ ምዕራባውያን በቀላሉ እንደማያዩት ነው የሚገለጸው።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top