“ነዳጅ ሲቀዳ ጥሬ ገንዘብ መቀበል አሁንም አልቀረም” - የመኪና ባለንብረት ተጠቃሚዎች

1 Mon Ago
“ነዳጅ ሲቀዳ ጥሬ ገንዘብ መቀበል አሁንም አልቀረም” - የመኪና ባለንብረት ተጠቃሚዎች
  • “ነዳጅ ሲቀዳ ጥሬ ገንዘብ መቀበል አሁንም አልቀረም” - የመኪና ባለንብረት ተጠቃሚዎች
  • "በአንዳንድ አካባቢዎች ኔትወርክ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ የጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል” - የነዳጅ እና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን

     *****************************

 በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ውሳኔ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ አማራጮች እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።  ባለስልጣኑ በቴሌ ብር እና  በተለያዩ ባንኮች በኩል ግብይቱን  በማስፈፀም ላይ ይገኛል።

የዲጅታል ክፍያ ግብይት ሒደቱ አስገዳጅ  ሆኖ በሕግ ቢደነገግም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ነዳጅ ማደያዎች ውስጥ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ እየተስተዋሉ መሆናቸውን ኢቢሲ ሳይበር አረጋግጧል፡፡ 

ኢቢሲ ሳይበር ያነጋገራቸው  የመኪና ባለንብረት ተጠቃሚዎች፤ አካውንታቸው ላይ ገንዘብ አለመኖር፣ የኔትወርክ ችግር እና በነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ዘንድ  የሚስተዋል ግዴለሽነት  በጥሬ ገንዘብ ለመክፈል ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ። 

የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች በበኩላቸው፤  ነዳጅ ከቀዱ በኋላ  ገንዘብ በአካውንታቸው  የሌለ ደንበኞች ስለሚመጡ በራሳቸው በመሙላት እንደሚያስተናግዷቸው ነው የገለፁልን። 

ይሁን እንጂ  ከሕግና ስርዓቱ ውጭ በጥሬ ገንዘብ አንደማይቀበሉም ነው የገለፁት።

ነዳጅን በቴሌብር እና ባንኮች ባዘጋጇቸው አፕሊኬሽኖች የመገበያየት ልምዱ እያደገ ነው የሚሉት በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ ውጤቶች ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ፣ አልፎ አልፎ በጥሬ ገንዘብ የመገበያየት አዝማሚያ መኖሩን አምነዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያየ ምክንያት ኔትወርክ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ እና ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረው የጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዲኖር ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል። 

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በየሳምንቱ በመነጋገር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። 

እስካሁን ማደያዎችን ኦዲት የማድረግ ስራ በመስራት በጥሬ ገንዘብ ግብይት የፈፀሙት ላይ እርምጃ መወሰዱንም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

ለአብነትም 80 ማደያዎች ላይ ለአንድ ወር ነዳጅ እንዳያገኙ ማድረጉን የሚያነሱት አቶ ለሜሳ ቱሉ፤ በአዲስ አበባ ብቻ 40 ነዳጅ ማደያዎች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

አንዳንድ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች የዲጂታል ግብይቱ እንደጠቀማቸው ገልጸው፤  በሀገር ደረጃም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው በመሆኑ ወደፊት ችግሮች እየተስተካከሉ እንደሚሄዱም ጠቁመዋል።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top