ፓስፖርት በሀገር ውስጥ እንዲታተም የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው - የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት

24 Days Ago
ፓስፖርት በሀገር ውስጥ እንዲታተም የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው - የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት

በተያዘው ዓመት ፓስፖርት ጠይቀው ይጠባበቁ ከነበሩ ዜጎች መካከል ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑት መስጠት መቻሉን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ገልጿል። 

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የፓስፖርት አገልግሎት አንዱ እና ዋንኛው ነው። ይሁን እንጂ የፓስፖርት አሰጣጥን በተመለከተ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተደጋጋሚ ይስተዋላል። ኢቢሲም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ተደጋጋሚ ዜናዎች መስራቱ ይታወሳል። 

በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሚነሱ ቅሬታዎች አንዱ መጉላላት ነው የሚለው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ያሬድ መንግሥቱ፤ እርሱ ራሱም ላላገኘው አገልግሎት ሁለት ቀን በሰልፍ መጉላላቱን ለኢቢሲ ሳይበር ተናግሯል። 

አገልግሎት ፈልጎ በፍጥነት ማግኘት ከባድ እንደሆነ የሚገልጹት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወ/ሮ መዓዛ ቅዱስ፤ በአንድ ቀን ጉዳይን ማከናወን ካለመቻሉም በላይ በሰልፍ ጊዜን አባክኖ አገልግሎቱን ሳያገኙ መመለስም እንዳለ ነው የሚናገሩት። 

አገልግሎት ለማግኘት መጠበቅ ግዴታ ሲሆንም፤ በተለይ ለአዛውንቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የወረፋ መጠበቂያ ቦታ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተገልጋዮች ጠቁመዋል። 

በተገልጋዮች የተነሱትን ቅሬታዎች ጨምሮ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት ስለመኖሩ የሚያምኑት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የኬላዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወንድሙ፤ ተጠቃሚውም ጋር የሚስተዋል የግንዛቤ እጥረት እንዳለ አንስተዋል። 

አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ወረፋ መጠበቅ የሚስተዋለው በአንድ በኩል በተገልጋዮች ዘንድ ባለው የቀጠሮ ቀንን አለማክበር ምክንያት ሲሆን፤ በሌላ በኩል በተቋሙ ባለው የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ውስንነት ጭምር መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል። 

በተቋሙ በኩል በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ የሚታዩ ውስንነቶችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን እና የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ችግርን ለመፍታትም እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አቶ ጌታቸው ወንድሙ ለኢቢሲ ሳይበር ተናግረዋል። 

ሙሉ ለሙሉ ችግሮች እስኪፈቱ በጊዜያዊነት በፈረቃ እስከ ምሽት ድረስ በመስራት ችግሮችን ለማቅለል እየተሞከረ መሆኑን፤ በተጨማሪም ፓስፖርት በሀገር ውስጥ እንዲታተም የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሂደት ሙሉ በሙሉ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን እና በተያዘው ዓመት ፓስፖርት ጠይቀው ይጠባበቁ ከነበሩ ዜጎች መካከል ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑት መስጠት መቻሉን ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም ፓስፖርት ለመውሰድ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስድ እንደነበር የሚናገሩት ዳሬክተሩ፤ አሁን ላይ ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ እየተሰጠ እንደሚገኝም አክለዋል። 

ከዚህ ቀደም በስራ ላይ የነበረው ቴክኖሎጂ ችግሮች እንዲባባሱ ያደረገ እንደነበር ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ስራ ሲገቡ እና የሰው ኃይል እጥረቱ ሲቀረፍ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚነሱ ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፉ ተናግረዋል። 

በሜሮን ንብረት


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top