ኢትዮጵያን ከዓለም ያስቀደመው የዜማ ሊቅ - ቅዱሥ ያሬድ

29 Days Ago
ኢትዮጵያን ከዓለም ያስቀደመው የዜማ ሊቅ - ቅዱሥ ያሬድ

“ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ እርሱን የመሰለ አልተገኘም!” የሚል ብሂል በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የሠፈረለት የሥድስተኛው ምዕት ዓመት የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ደራሲ፣ የዜማ ቀማሪ፣ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ይገልጻሉ፡፡

ቅዱስ ያሬድ ከሚታወቅበት የዜማ ሥራዎቹ በተጨማሪ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተያያዘ ሥራው ሊወሳለት የሚገባው እንደሆነም ይነገራል፡፡

የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ከድንጋይ ላይ ጽሑፍ ወደ ብራና ሽግግር ያደረገው ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክ እና ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ በተደረጉ የትርጉም ሥራዎች እንደሆነ ታሪክ ዋቢ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ በሥድስተኛው ምዕት ዓመት ከተነሣ በኋላ ያዘጋጃቸው እና የደረሳቸው አንቀጸ ብርሃን እና አምስቱ ዐበይት መጻሕፍት ማለትም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ መዋሥዕት፣ ዝማሬ፣ ምዕራፍ የመጀመሪያ ሀገራዊ ሥራዎች ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ከድንጋይ ላይ ጽሑፎች ወደ ብራና ሽግግር ሲደረግ ከቅዱስ ያሬድ የቀደመ ሥነ-ጽሑፍ እንደሌለ ጠቅሰው፣ "በዚህም ምክንያት የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ መሥራች ብቻ ከማለት ይልቅ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ መሥራች ልንለው ይገባል" ይላሉ፡፡ የዜማ ሥራዎቹን ስንመለከት ከደራሲነቱ ባሻገርም ለዝማሬ እንዲመች ምልክት (ኖታ) አዘጋጅቶላቸዋል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማ ከሚመራበቸው ሂደቶች አንዱ በመቋሚያ የሚደረገው ዝማሜ ሲሆን፣ ይህም አሁን ዓለም እየተጠቀመበት ያለው "ኮንደክቲንግ" መነሻ እንደሆነ እና ኢትዮጵያ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ለዓለም ያበረከተችው ትሩፋት መሆኑን የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ፈጣሪው ሙላቱ አስታጥቄ በምርምራቸው አረጋግጠዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም ነበር በአክሱም ከተማ የተወለደው፡፡ እናቱ ታውክሊያ ሲባሉ አባቱ ደግሞ ይስሐቅ ይባሉ እንደነበር ታሪኩ ያሳያል፡፡

አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበሩ፡፡ ያሬድ ሰባት ዓመት ሲሆነው አባቱ ስለሞቱበት እናቱ ት/ቤት ለማስገባት መምህር ጌዲዮን ወደሚባሉ አጎቱ ጋር ወሰዱት፡፡ በኋላም የብሉይ እና የሐዲስ መምህር ሆኖ በመምህሩ በጌዲዮን ወንበር ተተካ፡፡

ብሉይ እና ሐዲስን እያስተማረ እያለም አሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምትጠቀምባቸውን ዜማዎች አዘጋጀ፡፡ ዜማዎቹን ያዘጋጀው በሦስት ዓይነት ስልት(ኖታ) ሲሆን፣ እነሱም ግእዝ፣ ዕዝል እና ዓራራይ ይባላሉ፡፡ እነዚህ የዜማ ዓይነቶች የአንዱ ድምፅ ከሌላኛዉ ድምፅ ያልተደበላለቀ ወጥ የሆነ ድምፅ እንዳላቸው የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እና በዜማው ላይ ጥናት ያደረጉ ሌሎች ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ዜማዎቹ ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች ማለትም ለበጋ፣ ለክረምት፣ ለመጸው እና ለጸደይ እንደሚሆን አድርጎ ከፋፍሏቸዋል፡፡ ለየበዓላቱም ተስማሚ ድርሰት መድቦላቸዋል፡፡ ይህንን ድርሰቱን በግእዝ፣ በእዝል እና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀው ሲሆን፣ ለነዚህም አስር የዜማ ምልክቶች ሠርቶላቸዋል፡፡ እነዚህ ምልክቶችም ይዘት፣ ደረት፣ ቅናት፣ ጭረት፣ ድፋት፣ ቁርጥ፣ ሩጥ፣ ርክርክ፣ ሂደት እና ሰረዝ ይባላሉ፡፡ ምልክቶቹም የዜማዎቹን መውረድ እና መውጣት እንዲሁም መጥበቅ እና መላላት ከማመልከታቸውም ባሻገር፣ በትምህርት ሂደት የጠቋሚነት ሚና በመጫወት ለዜማዉ መጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ቅዱስ ያሬድ የተነሳው "ዘጠኙ ቅዱሳን" ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በዘጠኙ ቅዱሳን ከእብራይስጥ፣ ከአረማይክ እና ከዓረብኛ የተተረጎሙት ቅዱሳት መጻሕፍት በቅዱስ ያሬድ የድርሰት ሥራ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከመጻሕፍቱ ያገኛቸውን ምስጢራት ቃል በቃል እየጠቀሰ እንዲሁም ሐሳባቸውን ጨምቆ በመውሰድ በራሱ ቋንቋ እያራቀቀ ለድርሰቱ እንደተጠቀመባቸው ድርሰቶቹ ዋቢ ናቸው፡፡

ሙራደ ቃል በተባለ ቦታ ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲያዜም ንጉሱ አፄ ገብረ መስቀል ከነሠራዊቶቻቸው ንግሥቲቱ ከነደንገጡሮቿ፣ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ሊቃውንቱ እና ካህናቱ አየመጡ ያዳምጡ እንደነበር እና ንጉሡም በዚህ ምክንያት ቅዱስ ያሬድን በጣም ይወዱት እንደነበር ይነገራል፡፡ ከንጉሡ ጋር ያለው ቅርበትም ዜማውን በአጭር ጊዜ ለማስተማር እና በፍጥነት እንዲስፋፋ ለማድረግ አስችሎታል፡፡

በኋላም ንጉሡን አስፈቅዶ ለምናኔ ጉዞውን ከአክሱም ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ተራሮች አደረገ፡፡ በዚያም አሁን በስሙ የታነጸው ቤተ ክርስቲያን ባለበት ቦታ ላይ በምናኔ ተወስኖ ደብረ ሐዊ ከተባለው ተራራ ላይ ብዙ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ ከጸለምት ዋሻዎች በአንዱ ግንቦት 11 ቀን በ571 ዓ.ም እንደተሰወረ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ታስተምራለች፡፡ በዚህም ምክንያት በየዓመቱ ግንቦት 11 ቀን መታሰቢያውን ታከናውናለች፡፡

ቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችን ሲያዘጋጅ ከቅዱሳን መጻሕፍት የወሰዳቸውን ርእሰ ጉዳዮች በድርሰት ሥራዎቹ እንደ ፈርጥ ሲጠቀምባቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ ብሉያትን ከሐዲሳት፣ ከሊቃዉንት እያጣቀሰ ያለምንም ችግር የድርሰት ሥራዎቹን ያከናውን እንደነበር ድርሳናቱ ምስክሮች ናቸው፡፡ ድርሰቶቹ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ፣ የቃላት አመራረጡ፣ የዐረፍተ ነገር አወቃቀሩ፣ የሚስጥር እና የዘይቤ አገላለጹ ከፍተኛ የሥነ-ጽሑፍ ተሰጥኦ እንደነበረው ማሳያ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ በቅዱስ ያሬድ የተደረሱት የዜማ መጻሕፍት ስድስት ሲሆኑ፣ እነርሱም አንቀጸ ብርሃን፣ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ዝማሬ፣ መዋስዕት እና ምዕራፍ ይባላሉ፡፡

ከስድስቱ መጻሕፍቱ የዓመቱን በዓላት እና ሳምንታት መዝሙራትን ሰብስቦ የያዘው ድጓ ትልቁ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍ ነው፡፡

ጾመ ድጓ የሚባለውም ሌላው የዜማ መጽሐፍ ሲሆን ተጠንቶ ለመምህርነት የሚያበቃ ነው፡፡ድጓ ቁጥሩ ከአስተምህሮ ሲሆን፣ በዐቢይ ጾም የሚየሚዜሙ መዝሙራትን የያዘ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ነው፡፡ ሌላኛው ዝማሬ የሚባለው መጽሐፍ የምስጋና መዝሙራትን የያዘ ነው፡፡ መዋሥዕት ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት ለማድረስ በበዓላት እና በአጽዋማት ደግሞ የማለዳ ምስጋና የሚደርስባቸውን መዝሙራት የያዘ ነው፡፡ ምዕራፍ ከመዝሙረ ዳዊት የተውጣጣ ድርሰት ሲሆን፣ የዳዊት መዝሙራትን በየምዕራፉ እየከፋፈለ የዜማውን ዓይነትና ማሳረፊያ የሚገልጽ ነው፡፡ አንቀጸ ብርሃን ድንግል ማርያምን የሚያወድስ የፀሎት መጽሐፍ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ለቤተ ክርስቲያን ለሀገርም ያደረገዉ አስተዋጽኦ እጅግ በጣም የላቀ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዱ አገልግሎት የሚወሳ ነው፡፡ የቤተክርሰቲያኒቱ መምህራን ይንን ሲገልጹ "የቤተ ክርስቲያን አምድ፣ የውስጥ እና የውጭ መብራቷ፣ በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን መንቀሳቀሻ ሕይወት ነው" ይላሉ፡፡ "በድርሰቶቹ ውስጥ ያሉ መልዕክቶችም እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ፣ ከመጥፎ ነገር እንድንቆጠብ፣ በጎ ነገርን እንድንይዝ፣ ጥበብን እንድንፈልግ፣ ሰላም እንዲኖረን የሚያስተምሩ ናቸው" በማለት እንትት ሰው ወደ በጎ ነገር አንደሚመሩ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቅዱስ ያሬድ ብዙ የተጻፈለት፣ የሚጻፍለት፣ የተነገረለት እና የሚነገርለት ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ይገለጻል፡፡

በሀገር ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያ አሁን ከዓለም ቀድማ የራሷን የዜማ ስልት ከነቀመሩ እንዲኖራት ያስቻለ የሀገር ባለውለታ ነው፡፡ ከሙዚቃ አበርክቶውም ባሻገር በድረሰት ሥራዎቹ የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ አባት ሊያስብሉት የሚችሉ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡

ይህንን አበርክቶውን መሰረት በማድረግም በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 1963 ዓ.ም በስሙ የሚጠራ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተከፍቷል፡፡ የሙዚቃ ት/ቤቱ ሲመረቅ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ "ይህ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም ያስቻለን ምክንያት ለውጭው ሀገር ት/ቤት ብቻ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ የሀገራችን የዜማ ባሕል እና ሥነ ሥርዓት ተጠብቆ በዚህ እንዲደራጅ በማሰብ ነው" በማለት ትምህርት ቤቱ የተከፈተበትን ምክንያት ገልጸው ነበር፡፡

ዓለምን ቀድሞ በ6ኛው ክፍለ ዘመን የዜማ ምልክቶችን ያበረከተው የቅዱስ ያሬድ አጻጻፍ እና አቀራረቡ ከ16ኛ ክፍለ ዘመን በኋላ ከተነሱት የሙዚቃ ጸሐፊዎች እና ኮንዳክተሮች እነ ሐንድል፣ ቤቶቨን፣ ሃይድን እና ሞዛርት ጋራ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሁን እና ለኢትዮጵያም ሆኖ ለዓለም ያበረከታቸው ሥራዎች የሚገባውን ያክል እንዳልተዘከረ የሙዚቃ ባለሙያዎች በቁጭት ያወሳሉ፡፡ 

በለሚ ታደሰ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top