በቤንሻንጉል፣በጋምቤላ፣በሐረሪ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል፡- የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

3 Mons Ago 366
በቤንሻንጉል፣በጋምቤላ፣በሐረሪ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል፡- የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
 
በክልሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁንም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስታውቋል።
 
በቤንሻንጉል፣በጋምቤላ፣ በሐረሪ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ በአንድ ጊዜ እንደሚካሄድ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
 
በክልሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን ቀድሞ ለመጀመር ዕቅድ እንደነበር የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤በአንዳንድ ምክንያቶች የተወሰነ መዘግየት መኖሩን አስታውቀዋል።
 
በተለይ የስምንተኛ እና የሥድስተኛ ክፍል ፈተናዎች መጀመር በክልሎች አጀንዳ የማሰባሰቢያ ቀኑ በተወሰ መልኩ እንዲገፋ ተደርጓል ተብሏል።
 
በሦስቱ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ በቅርብ ቀናት እንደሚሰበሰብ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል።
 
በዚህም በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ በሐረሪ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ በቀጣይ ሳምንት በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
 
አጀንዳ የማሰባሰብ ክንውኑ በአብዛኞቹ ክልሎች እስከ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑ ተገልጿል።
 
በአፋር ክልል ያለው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ከባድ ሙቀት ያለበት በመሆኑ፤ በክልሉ የሚከናወነው አጀንዳ ማሰባሰብ ጥቅምት አካባቢ እንደሚካሄድ ይፋ ተደርጓል።
 
በአማራ ክልል ከ200 በላይ ተባባሪዎች የሰለጠኑ ሲሆን፤ በክልሉ አስቻይ ሁኔታዎች እስኪሟሉ ድረስ ተጨማሪ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።
 
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን በማድረግ ሁኔታዎችን መመልከት መቻሉን በመግለጽ፤ስራውን ለመጀመር ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ ቀሪ ስራዎች እስከሚጠናቀቁ እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል።
 
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተከናወነው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በርካታ ልምድ ማግኘቱ የተጠቀሰ ሲሆን፤በቀጣይ በክልሎች በሚካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በአዲስ አበባ የነበሩት ችግሮች እንዳይደገሙ ይሰራል ተብሏል።
 
በተስፋዬ ጫኔ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top