በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው የ45 ሰዎች ህይወት አለፈ

1 Mon Ago 271
በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው የ45 ሰዎች ህይወት አለፈ

በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ፍልሰተኞችን አሳፍረው የነበሩ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው ቢያንስ 45 ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች መጥፋታቸው ተገልጿል፡፡

310 ፍልሰተኞችን አሳፍረው ከየመን የተነሱ ሁለት ጀልባዎች በደቡብ ምዕራብ ጅቡቲ የባህር ዳርቻ ከደረሱ በኋላ መስጠማቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል፡፡

በድርጅቱ ድጋፍ ከሰኞ ጀምሮ በተከናወነ የፍለጋ ስራም በሕይወት የተረፉ 115 ሰዎችን ማዳን መቻሉን የጅቡቲ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ገልፀዋል።

ከፍልሰተኞቹ መካካል እስከ አሁን ድረስ 61 የሚሆኑት የደረሱበት አለመታወቁ የገለፁት የጠረፍ ጠባቂው፤ ፍለጋው በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል፡፡

ጀልባዎቹ የሰመጡት በጅቡቲ ሰሜናዊ ምዕራብ ሖር አንጋር ክልል አቅራቢያ ካለ የባህር ዳርቻ በ150 ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን የጠረፍ ጠባቂው አክለዋል።

የጠፉትን ለማግኘት እና የተረፉትን ፍልሰተኞች ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።

የድርጅቱን መረጃ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ከአፍሪካ ቀንድ ተነስተው በየመን በኩል የሚያቀኑ ፍልሰተኞች ቁጥር በፈረንጆቹ 2022 ከነበረበት 73 ሺህ ወደ 97 ሺህ 200 ደርሰዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top