የተቀበረውን የጥቁሮች ታሪክ ሲፈልጉ የኖሩት ምሁር - ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ

1 Mon Ago 861
የተቀበረውን የጥቁሮች ታሪክ ሲፈልጉ የኖሩት ምሁር - ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ

 

በታሪክ፣ በፖለቲካ እና በባሕል ረገድ ሀገርን በሚያስተዋውቁ ፊልሞቻቸው ይታወቃሉ። ሥራዎቻቸው በአፍሪካ ማንነት፣ በቅኝ ግዛት ተፅዕኖ እና በማኅበራዊ ፍትሕ ላይ ያተኮሩ ናቸው። 

ለበርካታ አሥርት ዓመታት በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ፕሮፌሰር ሆነው እየሠሩ ሲሆን፣ የጥቁር እና የአፍሪካ ፊልም አዘጋጆችን በማስተማር እና በማበረታታት ይታወቃሉ። 

በሥራዎቻቸው ከአፍሪካ ታላላቅ የፊልም አዘጋጆች መካከል አንዱ ሊሆኑ ችለዋል። በፊልሞቻቸው የተደበቁ እውነተኛ የአፍሪካ ታሪኮችን ይተርካሉ። ሆሊውድ የጥቁር እና የአፍሪካን ታሪክ የሚወክልበትን መንገድ ይሞግታሉ።

ፊልሞቻቸው በጥቁሮች ታሪክ ጥናት ላይ ለሚሠሩ በመላው ዓለም ውስጥ ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት እና ግለሰቦች ግብዓት ሆነዋል። በሎሳንጀለስ የሚገኘው የአፍሪካ-አሜሪካውያን ጥቁሮች ፊልም ትምህርት ቤት መሥራችም ናቸው።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የተወለዱት የካቲት 25 ቀን 1938 ዓ.ም በገንደር ነው። በሠሯቸው ታላላቅ ሥራዎችም ታዋቂ የፊልም ባለሙያ እና የአርት ኮሌጅ ፕሮፌሰር ለመሆን በቅተዋል። በሎስ አንጀለስ የጥቁሮች ፊልም ትምህርት ቤት ውስጥ አንቱ የተባሉ የፊልም ባለሙያ ናቸው።

ለቤተሰቦቻቸው ከአስር ልጆች መካከል አራተኛ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፣ ለትምህርት እና ለኪነ ጥበብ ሥር የሰደደ ፍቅር ካለው ቤተሰብ ነው የተገኙት። እናታቸው የአንደኛ ደረጃ መምህርት ነበሩ። አባታቸው ደግሞ የተውኔት እና ቴአትር ደራሲ እና አዘጋጅ የነበሩ ሲሆን፣ ትንሹ ኃይሌ የሕይወት መንገዱን ያገኘበትን የዳንስ ቡድን አቋቁመው ነበር። ትንሹ ኃይሌም በአባቱ ሥራዎች ይለማመድ ነበር። በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ነባር ብሂሎች እና ታሪኮች እየሰሙ ማደጋቸው ለኋላው ሕይወታቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገ የይነገራል።

በ1959 ዓ.ም ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ወደ አሜሪካ አቀኑ። መጀመሪያ ላይ በቺካጎ፣ ኢሊኖይ በሚገኘው ‘ጉድማን’ ቴአትር ቤት የዳይሬክተርነትን እና ተዋናይነት ኮርሶችን ወስደዋል። በኋላም ወደ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሎስ አንጀለስ (UCLA) በመግባት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፊልም ዝግጅት አግኝተዋል። 

በጅማሮአቸው አካባቢ ሕይወት በአሜሪካ አልጋ በአልጋ አልሆነችላቸውም። በተለይም የልጅነት ሕልማቸውን ለማሳካት የተፈተኑት ፈተና እና ፅናታቸው ለስኬታቸው መሠረት ሆኗቸዋል። ወደ ፊልሙ ዓለም ሲገቡ ሆሊውድ ፊት መንሣቱ እና ፊልም ለመቅረጽ የሚደግፋቸው ማጣታቸው ከባዱ ፈተናቸው ነበር።

እንደምንም ብለው ፊልማቸውን ቀርጸው ለእይታ ሲያበቁ ደግሞ የሚያሳዩበት ሲኒማ ቤት ማጣታቸው የነበረባቸውን ተፅዕኖ ከባድነት የሚያሳይ ነው። ቪዲዮ አከራዮችም ፊልማቸውን በመደብራቸው እንደማያስቀምጡላቸው ይነግሩአቸው ነበር። 

ነገር ግን ለእነዚህ ፈተናዎች እጅ ሳይሰጡ የራሳቸውን የፊልም አከፋፋይ ድርጅት አቋቋሙ። ከራሳቸውም አልፎ አፍሪካውያን ፊልም ሠሪዎችን ለማበረታታት የፊልም እና መጽሐፍት መደብር ከፍተው እንደ እርሳቸው ጀማሪ ሆነው መንገዱ የጠፋባቸውን አፍሪካውያንን እና አፍሪካ-አሜሪካውያንን አበረታትተዋል።

በርካታ ዐይነ-ገብ ሥራዎችን ሠርተው ለተመልካቾች አቅርበዋል። ‘Bush Mama’ በሚል ርዕስ ለሕዝብ ያቀረቡት ፊልም በአሜሪካ ስላሉት ጥቁሮች ተጋድሎ፣ ሥርዓታዊ ዘረኝነት እና ስለ ማኅበራዊ ኢ-ፍትሐዊነት የሚገልጽ ታላቅ ፊልም ነበር።

"Harvest: 3000 Years" የተባለው ፊልማቸው ደግሞ በኢትዮጵያ የነበረው የፊውዳል ሥርዓት ሕዝቡ ላይ ሲያደርሰው የነበረውን ጫና የሚተች ሲሆን፣ የበርሊን ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።

"ሰንኮፋ" መለያቸው እስከሚሆን ድረስ የሚታወቁበት ፊልም ነው። አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ስለነበረው የባሪያ ንግድ በሚገልጽ ጠንካራ ታሪክ የተዋቀረው “ሰንኮፋ”፣ የተቀረፀው በጋና በሚገኘው ኤልሚና የባሪያ ንግድ ግንብ ውስጥ ነበር። ታሪኩ የሚያጠነጥነው በዐይነ ህሊናዋ ወደ ኋላ በመጓዝ የባሪያ ንግድ ምን ይመስል እንደነበረ በምታሰላስል አንዲት አፍሪካ-አሜሪካዊት ሴት ላይ ነው። ፊልሙን ሆሊውድ ባይቀበለውም፣ በግላቸው አሰራጭተው አድናቆትም አትርፈውበታል።

“ሰንኮፋ” በምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ የአፍሪካ ታላቅ ፊልም ፌስቲቫል (FESPACO) ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። ለዕይታ እንደበቃ አከፋፋይ በማጣቱ ራሳቸው በ35 አገራት በመዞር ያሳዩት “ሰንኮፋ” ከአራት ዓመት በፊት በኔትፊልክስ በኩል በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንገድም፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ ለሚገኙ ተመልካቾች ቀርቧል። ይህም ፊልሙ ከተሠራ ከ28 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።

ከ1970ዎቹ አስከ 1980ዎቹ በነበረው የደርግ ሥርዓት ወቅት ወደ ሀገሩ ስለተመለሰ ኢትዮጵያዊ ምሁር ከፊል ታሪክ የሚያትተው ፊልማቸው ደግሞ "ጤዛ" ነው። “ጤዛ” በቬኒስ ፊልም ፌስቲቫል የተሻለ ስክሪንፕሌይ እና ልዩ የዳኞች ሽልማትን አሸንፏል። 

ከቢቢሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “Imperfect Journey” የተሰኘውን እና በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ የፖለቲካ ጎዞ እና "ቀይ ሽብር"፣  ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ ደግሞ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ እና ሥነ-ልቦና ማገገም የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም ነው። 

በአሜሪካ ከተማዎች የሚገኙ የጥቁሮችን ጉዞ የሚተርከው የሁለት ሰዓታት ቆይታ ያለው “Ashes and Embers” የሚል ስያሜ ያለው ዘጋቢ ፊልማቸው የማንነት እና የነጻነት ጽንሰ ሀሳቦችን የያዘ ነው። ፊልሙን አባቶቻችን ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ያደረጉትን ተጋድሎ ለማሳየት እና በታሪክ ውስጥም ለማሳወቅ በማሰብ እንደሠሩት ይነገራል።

“After Winter: Sterling Brown” በሚል ርዕስ የሠሩት ዘጋቢ ፊልም ስለታዋቂው ጥቁር አሜሪካዊ ገጣሚ እና ተዋናይ ስተሪሊንግ ብራዎን ሥራዎች ያቀረቡበት ነው።

“Adwa: An African Victory” በሚል ርዕስ ደግሞ ኢትዮጵያ ቅኝ ሊገዛት በመጣው ጣሊያን ላይ የተቀዳጀችውን ድል እና ድሉ እንዴት ለፍሪካውያን የነጻነታቸው እንቅስቃሴ ስንቅ እንደሆናቸው የሚያሳይ ነው።

ፕሮፈሰር ኃይሌ ገሪማ የአፍሪካ ሲኒማ ራሱን ችሎ እንዲቆም ይሟገታሉ። ሆሊውድ ከአፍሪካ አንጻር የሚከተለውን ትርክት የማይቀበሉ ከመሆናቸውም በላይ አጥብቀው ይተቹታል። ለአፍሪካ ፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት ከመሟገት አልፈው ተግባራዊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም የአፍሪካ የፊልም ሠሪዎችን የሚደግፍ ‘Mypheduh Films’ ሚባል ነጻ የፊልም ስርጭት ኩባንያ አቋቁመዋል።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ስለኢትዮጵያ

በየአጋጣሚው ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ለሚሉት ሰዎች፣ "ስለኢትዮጵያ ሳስብ አልደነግጥም፤ የቆምኩበትን የአባቶቼን መሠረት አውቀዋለሁ! ኢትዮጵያ ባንተ አልተጀመረችም ባንተ አትጠፋም!" በማለት ነው ምላሽ የሚሰጡት። የኢትዮጵያ ታሪክ መሠረት ያለው መሆኑን ሲያወሱም፣ “ታሪክ የሌለው ህዝብ እና ስር የሌለው ዛፍ አንድ ናቸው” ይላሉ። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ኅብረት ውጤት መሆኑን ሲያወሱም፣ “ዓድዋ ላይ ምኒልክን ተከትሎ የወጣው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፤ ለዚህ ነው ያሸነፍነው፤ በማይጨው ጊዜ ብትንትናችን ወጥቶ ነበር፤ ለዚህ ነው የተሸነፍነው። ይህ ቅልጥጥ ያለ እውነት ነው!“ ብለዋል። "ብዙ ኢትዮጵያውያን እኔ የተማርኩና ትልቅ ደረጃ ስለደረስኩ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ያለብኝ እኔ ነኝ ይላሉ፤ ነገር ግን ለትውልድ የምናስብ ከሆነ ማዳበሪያ ሆነን ለመጪው ትውልድ የሚሆን ዘር ማፍራት አለብን፤ ይህ ግን ቁርጠኝነትን ይጠይቃል" በማለት ነው ለዛሬው ስሜታችን ሳይሆን ለትውልድ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት። "ኢትዮጵያዊነት ማንም ለማንም የሚያድለው ሳይሆን መከባበር እና ሁሉን አካታችነት ነው" በማለትም የኢትዮጵያን ሕብር ይገልጻሉ።

በሥራዎቻቸው በርካታ ታላላቅ ሽለማቶችን አግኝተዋል። እ.አ.አ በ1976 በዘጋቢ ፊልም ዘርፍ የ‘ሚቼክስ አዋርድ’ን ወስደዋል፤ በፓን አፍሪካ የፊልም እና ቴሌቪዥን ፌስቲቫል ላይ ደግሞ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር ተብለው ተሸልመዋል። እ.አ.አ በ1993 በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው “The Mayor's Arts Awards in Washington, DC” የላቀ አርቲስቲክ ዲሲፒሊን ተሸላሚ ነበሩ። የፓን አፍሪካን የፊልም ባለሙያዎች ኮሚቴ አባል ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የዕድሜ ልክ ስኬት ተሸላሚ ሲሆኑ በዚህ ስርም፡-

  • Smithsonian African American Film Festival – Legacy Award (2018)
  • Film at Lincoln Center – Tribute to Haile Gerima (2021)
  • Locarno Film Festival – Pardo alla Carriera (Lifetime Achievement Award) (2021)

ሽልማቶችን ያገኙ ጉምቱ ፓን አፍሪካኒስት ናቸው።

የ79 ዓመቱ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ አሁንም የአፍሪካን ባህል፣ የነጻነት ተጋድሎ እና የቅኝ ግዛት ጫና እንዲሁም የጥቁሮችን ሥርዓት ወለድ ጭቆና የሚያጋልጡ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ። ያኔ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ሲገቡ ማረፊያ ያጡ ፊልሞቻቸው ዛሬ በእነኔትፍሊክስ ተለምነው ለተመልካቾች እየቀረቡ ናቸው። በዚህም ለፈተናዎች እጅ ሳይሰጡ የራሳቸውን የስኬት ጎዳና ያበጁ ለመሆን በቅተዋል።

በአሁኑ ጊዜም ላለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ ሲለፉበት የነበረው "ጥቁር አንበሳ የሮማን ተኩላ ሲይዝ" የሚል ፊልማቸውን እያገባደዱ ነው። ይህ ፊልም የቅኝ ግዛት ሥርዓት የአፍሪካን ሥልጣኔ እንዴት እንዳጠፋው የሚያትት በመሆኑ እያንዳንዱ ታሪክ ከዋናው ምንጭ እንዲካተትበት ተብሎ ይህ ሁሉ ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል።

በለሚ ታደሰ

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top