በአዲስ አበባ ከተማ የ2018 ዓ.ም የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ እንዲያደርጉ ከተፈቀደላቸው የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ በጭማሪው ላይ ከስምምነት ያልደረሱ 21 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ጉዳይ በአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላላም ሙላት (ዶ/ር) ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ ደምብን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 1ሺህ 585 የግል ትምህርት ቤቶች መካካል ከሁለት ዓመት በፊት የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ያላደረጉ 1ሺህ 200 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የ2018 ዓ.ም የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ እንዲያደርጉ እንደተፈቀደላቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ጭማሪው የሚወሰነው በወላጆች እና በትምህርት ቤቱ መካከል በሚደረግ ውይይት እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህም በከተማዋ ካሉ ትምህርት ቤቶች 79 በመቶ የሚሆኑት ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ስምምነት ላይ ያልደረሱት የቀሪዎቹ ጉዳይ በአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ታይቶ የሚወሰን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ካቢኔ ባፀደቀው የግል ትምህርት ቤቶች የአገልግሎት ክፍያ ደምብ መሰረት፣ ትምህርት ቤቶቹ ባላቸው ደረጃ ከ0 እስከ 65 በመቶ ባለው የክፍያ ጭማሪ ጣሪያ ከወላጆች ጋር ተወያይተው መጨመር እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ እስከ 65 በመቶ የክፍያ ጭማሪ ጣሪያ የተወሰነለት ደረጃ 4 ላይ የሚገኘው ዳይመንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ ነው ሲሉም አያይዘው ተናግረዋል፡፡
አሁን ጭማሪ የሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች እስከ 3 ዓመት ሌላ ጭማሪ ማድረግ አይችሉም።