የብሪክስ መሥራች እና የ17ኛው ብሪክስ ጉባኤ አዘጋጅ የሆነችው ብራዚል በአሁኑ ፕሬዚዳንቷ መሪነት ተዓምር የተባለለት የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ሀገር ነች፡፡
ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ከአውሮፓውያኑ 2003 እስከ 2010 በሁለት ዙር ብራዚልን መርተዋል፡፡ በሦስተኛው ዙር ደግሞ ከ2023 እስከ አሁን እየመሯት ይገኛሉ፡፡
79 ዓመት የሆናቸው ሉላ በአውሮፓውያኑ ጥር ወር 2003 ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ብራዚል በማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ውስጥ የነበረች ቢሆንም፣ ከባድ ፈተናዎች እና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ስጋት ገጥሟት ነበር።
የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥጥር ውጭ ያልነበረ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚው ዕድገት እያሽቆለቆለ ብራዚልን ከፍተኛ የውጪ እዳ ውስጥ ከቷት ነበር።
ሁኔታው እየከፋ ሄዶም ሀገሪቷን ቀውስ ውስጥ በመክተቱ የፖለቲካዊ ለውጥ ፍላጎቱን ናረ። በወቅቱም የፕሬዚዳንት ሉላ ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ የሕዝቡ ፍላጎት ቢሆንም፣ ፓርቲው አክራሪ ሶሻሊስት ሆኖ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ አደጋ ውስጥ ያስገባል የሚል ፍርሃትም እንዣብቦ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ዝቅተኛ ገቢ፣ የእዳ ጫና፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ማሽቆልቆል እና የድህነት መንሰራፋት ቀጠለ።
ሀገሪቷ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ነበር ሉላ ዳ ሲልቫ በ2003 በምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን የመጡት፡፡ ታዲያ ዳ ሲልቫ የብራዚል ምጣኔ ሀብት ላይ ምን አይነት ለውጥ አመጡ?
ሉላ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ማኅበራዊ አካታችነት እውን ያደረጉ ሲሆን፣ ያ ዘመን በብራዚላውያን ዘንድ "ወርቃማ ዘመን" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
የብራዚል ዓመታዊ ዕድገት በአማካይ ከ4 በመቶ በላይ እንደረሰ የዓለም ገንዘብ ድርጅት ሪፖርት አመላክቷል፡፡ በዚህም 558 ቢሊዮን ዶላር የነበረውን ጂዲፒ በ2010 ወደ 2.2 ትሪሊዮን ዶላር አድጓል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የተከተሉት የዕድገት ሞዴል ቀደም ሲል ቀውስ ውስጥ የነበረውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ብራዚልን የተስፋ ምድር አደረጋት።
እንደ ብረት፣ አኩሪ አተር ዘይት እና ሌሎች የብራዚልን ጥሬ እቃዎች እና ማዕድናትን ቻይናን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ዋነኛው ምክንያት ነበር።
የሉላ መንግሥት ከቀድሞ መንግሥት የወረሰውን የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ በመንተራስ የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ፣ ምንዛሬን በገበያ እንዲመራ በማድረግ እና ምርታማነት ላይ በመመሥረት የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ቻለ።
ብራዚል የውስጥ በጀቷን በእራሷ ከመሸፈን አልፋ ከዕቅዷ ሁለት ዓመት ቀድማ በ2005 በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የነበረባትን ዕዳዋን ሙሉ በሙሉ መክፈል ችላለች።
ሀገሪቱ የውጪ እዳዋን በእጅጉ ቀንሳ የውጭ ምንዛሪ ክምችቷን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራ የኢኮኖሚ ችግሯን አሻሻለች።
ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ ሲሄድም በሚልዮን የሚቆጠሩ አዳዲስ መደበኛ ሥራዎች የተፈጠሩ ሲሆን፣ ሥራ አጥነትም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።
ዝቅተኛ ገቢ የነበራቸው ቤተሰቦች ገቢ እየጨመረ በመሄዱ የመግዛት አቅም ጨምሯል።
አካታችነት፣ የድህነት ቅነሳ እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ትልቁ የሉላ ዳ ሲልቫ መንግሥት ስኬት ነው፡፡
የግለሰቦች እና ቤተሰብ ገቢ እየጨመረ በመምጣቱ እና የገንዘብ ስርጭቱ ፍትሃዊ እየሆነ በመምጣቱ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብራዚላውያን ከድህነት ተላቅለው ወደ መካከለኛ የኑሮ ከፍ አሉ።
የብራዚል የውጪ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ተመንድጎ በ2003 እርሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከነበረበት 72.8 ቢሊዮን ዶላር በ2010 ወደ 200.4 ቢሊዮን ዶላር አድጓል።
ሪል እስቴትን ጨምሮ የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋጋ የተሻሻለ ሲሆን፣ ዜጎች ሀገር ውስጥ ለሚሠሩት ሥራ ያለ አድልኦ ብድር እንዲያገኙ መንገድ በመከፈቱ በርካቶች ቋሚ ሀብት መፍጠር ችለዋል፡፡
ይሁንና ሉላ ዳ ሲልቫ ከ2010 ጀምሮ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ተነስተው ክስ ተመስርቶባቸው ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡
እርሳቸው ከሥልጣን ተወግደው በቆዩባቸው 13 ዓመታት የብራዚል ኢኮኖሚም እንደ ፖለቲካው ምስቅልቅል ውስጥ ገብቶ ነበር የቆየው፡፡
ሉላ በጥር 2023 ዳግም ወደ ሥልጣን ሲመለሱ የብራዚል ኢኮኖሚ ከ2003 እስከ 2010 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም አደገኛ እና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ነበር።
በ2014 እስከ 2016 ከባድ የኢኮኖሚ ድቀት በኋላ የብራዚል የኢኮኖሚ እድገት ለአሥር ዓመታት ያህል ሲያሽቆለቁል የነበረ ሲሆን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢው ግን እንዳልተለወጠ መረጃዎች ያሳያሉ።
አጠቃላይ የመንግሥት ዕዳ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ የነበረ ሲሆን፣ ይህ የእዳ ጫና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም እያዳከመ መጣ።
በሉላ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናት የተሳካው የድህነት ቅነሳ ወደ ኋላ ተመልሶ ማኅበራዊ ሴፍቲ ኔት በመዳከሙ ብራዚል ወደምትታወቅበት ከፍተኛ ረሃብ መመለስ ጀምራ እንደነበር ኮቪንግተን የተባለ የመረጃ ምንጭ ያመላክታል።
ፕሬዚዳንቱ ዳግም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት እና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችን በማሻሻል ያተኮረ ሥራ እየሠሩ ነው።
በ2023 ሥራ ሲጀምሩም የብራዚል ዓመታዊ ጥቅል ምርት (GDP) ዕድገት በ2.9 በመቶ ወርዶ የነበረ ሲሆን፣ እርሳቸው ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ በ2024 በ3.4 በመቶ ከፍ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በዚህም መሰረት ከ2023 በፊት 1.96 ትሪሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረው የሀገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርት በ2024 ወደ 2.18 ትሪሊዮን ዶላር አድጓል፡፡
ሉላ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ሰፊ የሥራ ዕድሎች እየተፈጠሩ የሥራ አጦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ዝቅ እያሉ መጥተዋል።
ኢትዮጵያ ከሉላ ዳሲልቫ የዕድገት ሞዴል ምን ትማራለች?
ፊውቸር አፍሪካ የተሰኘው ድረገጽ ላይ "የመሰረተ ልማት ግንባታ በኢትዮጵያ አካታች ዕድገት ያመጣ ይሆን?" በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያወጡት ብሌሲንግ ቺፓንዳ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ በ2023 የ7.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡
ቺፓንዳ በጽሑፋቸው የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የኢትጵያ ሕዳሴ ግድብ ባሉ ታላላቅ መሰረተ ልማት ላይ አተኩራ እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው ይላሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ብራዚል ተአምር እንድትፈጥር ያደረጉበት የዕድገት ሞዴል ከሌላ የኮረጁት ሳይሆን በሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ላይ የቀረጹት ነው፡፡
ዳ ሲልቫ በተለይም ከ2003 እስከ 2010 የተጠቀሙበት ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት እና ጠንካራ ማኅበራዊ አካታችነት ኢትዮጵያ እየተከተለችው ካለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግብርናን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሠራች ያለውን ሥራ የሚጠቅሰው የዓለም ባንክ ይህ አካሄድ የዝናብ ወቅት ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረውን ግብርና እየለውጠው መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ባለ ብዙ ዘርፍ የዕድገት አቅጣጫን የምትከተል ሲሆን፣ ማዕድን፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አይ ሲቲ እና ቱሪዝም የኢኮኖሚ ዕድገቷ ምሰሶዎች ናቸው፡፡
ብራዚል ፈጣን ዕድገት ለማምጣት የተከተለችው የዕድገት ሞዴልም ተመሳሳይ ነው፡፡ ማኅበራዊ ጥበቃ፣ ድህነት ቅነሳ፣ ምርትን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት እና ውጤታማ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ትኩረት አድርጋባቸው የነበሩ ናቸው።
በመሆኑም ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ሰፊ ማህበራዊ አካታችነትን አጣምራ ስኬት ያስመዘገበችው ብራዚል ልምዷ ለኢትዮጵያ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው፡፡
ብራዚል የራሷን የዕድገት ሞዴል ተከትላ ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣችው ሁሉ ኢትዮጵያም ከከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ወደ ማንሰራራት እየመጣች ያለው ከሌሎች በቀዳችው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሰይሆነ ጫናን ተቋቁማ ተግባራዊ ባደረገችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ነው።
በለሚ ታደሰ