በጣና ሀይቅ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተገዝታ ወደሀገር ውስጥ የገባችውና የተለያዩ ከተሞች አቋርጣ አገልግሎት ወደምትሰጥበት የጣና ሀይቅ እየተጓጓዘች ያለችው ጣናነሽ ሁለት ጀልባ የዓባይን በረሀ እያቋረጠች ትገኛለች።
ይህ በእንዲህ እያለ ብዙ ኪሎሜትር በየብስ ላይ ተጉዛ እንድትሄድ መደረጉን በማስመልከት የተነሱ የአዋጭነትና አንዳንድ ጥያቄዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲን ኢቢሲ ዶትስትሪም አነጋግሯቸዋል።
በቅድሚያ የጀልባዋን አካላት ለትራንስፖርት በሚመች መልኩ ለያይቶ በማምጣት በሀገር ውስጥ መገጣጠም አይቻልም ነበር ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦
ይህን አይነት ትላልቅ ጀልባዎችን አካላትን መገጣጠም የሚችል በሙያው የሰለጠነ የሰው ሀይል ባለመኖሩ ይህ መሆን እንዳልቻለ ተናግረው የደኅንነት ችግር እንዳይገጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚገባ በመኪና ማጓጓዙ ተመራጨ መሆኑን ነግረውናል።
እንዲህ ያለው ተሞክሮ በመሬት በተከበቡ ሌሎች ሀገራትም ትላልቅ ጀልባዎችን ዲዛይን አድርገው ከሰሯቸውና በሙያው ልዩ ስልጠና ከሌላቸው ባለሙያዎች ውጭ ዳግም ለመገጣጠም በሚሞከርበት ወቅት ከጀልባዎቹ ውስብስብ አሰራር አኳያ ትልቅ ብልሽት ያጋጥማል በማለት ተናግረዋል።
አቶ ደምስ አያይዘውም የጀልባ አካላትን ለያይቶ ማምጣትና ገጣጥሞ በጥቅም ላይ ማዋል የአገልግሎት ዘመናቸውን ከማሳጠርም ባለፈ ለትልቅ አደጋና ብልሽት የሚዳርግ እንደሆነ ገልፀዋል።
እንደ ስዊዘርላንድ ባሉ የሰለጠኑ ሀገሮችም ትላልቅ የትራንስፖርትና የቱሪስት ጀልባዎችን ክፍሎች ለያይቶ ከማምጣት ይልቅ በየብስ ትራንስፖርት አጓጉዘው አገልግሎት ወደሚሰጡበት የውሀ አካል መውሰድ ተመራጭ እንደሆነ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።
ይህም ሲሆን ከረጅም ጊዜ አገልግሎት አኳያ፣ ከፍተኛ የዘርፉ አማካሪዎች ለረጅም ጊዜ የአዋጭነት ጥናት ተደርጎ እና ከአለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር ጀልባዋ በየብስ ተጓጉዛ ወደሚፈለገው ቦታ እንድትደርስ መወሰኑን ገልፀዋል።
በቀጣይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚያካልላቸው የውሀ ክፍሎች፣ በባሮ ሀይቅ ላይ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አነስተኛ ጀልባዎችን ለማሰማራት መታቀዱን ተናግረዋል።
ይህንንም በስፋት ለማድረግ እንዲቻል ቀላል ጀልባዎችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ማዕከል እንደሚከፈትና ባለሙያዎችንም ከሀገር ውጭ አሰልጥኖ በማምጣት በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል።
ይህ እስኪሆን ድረስ ግን በተለይ እንደጣናነሽ አይነት ዘመናዊ እና ግዙፍ ጀልባዎችን ለማጓጓዝ ያለው አማራጭ በየብስ አሁን እየተደረገ እንዳለው መሆኑ የጠቆሙት አቶ ደምስ ወደፊት ግን በዚህ ዘርፍ ያለውን የሀገር ውስጥ አቅም ለማሻሻልና ለማሳደግ እንደታሰበ ገልፀውልናል።
ጣናነሽ ሁለት በሀገራችን እስከዛሬ ካሉት የትራንስፖርትና የቱሪስት ጀልባዎች በላቀ ሁኔታ እጅግ ዘመናዊ እና ግዙፍ ጀልባ መሆኗ ይታወቃል።