የዓባይ - ዘመን አይሽሬ ውበት እና ጉልበት በጂጂ አንደበት

14 Hrs Ago 624
የዓባይ - ዘመን አይሽሬ ውበት እና ጉልበት በጂጂ አንደበት

ዓባይ ለኢትዮጵያውያን የክብራቸው ጌጥ፣ የኩራታቸው ምንጭ፣ የመመኪያቸው ዘውድ፣ የቅኔያቸው ሰም እና ወርቅ፣ የዜማ እና የግጥማቸው አቡጊዳ እንዱሁም የሥልጣኔያችን ምንጭ ማሳያ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በጭንቅ እና በጣር ወልደው ጥረው ግረው፣ ሁለት ሦስት መልክ አውጥተው ያሳደጉት ነው ዓባይ ለኢትዮጵያውያን።

ይሁንና ያሳደጉት ልጅ ፊቱን ሲያዞር የሚያንገበግበውን ያህል ዓባይ ከኢትዮጵያ መሬት ፈልቆ አንዳች ጥቅም ሳይሰጥ በመቆየቱ ሲያስቆጨን ኖሯል።

የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) “ዓባይ” ሙዚቃ የኢትዮጵያውያንን ቁጭት በአደባባይ የገለጠ ጉልበታም የኪነ-ጥበብ ሥራ ነው።

ዓባይ ለረሃብ እና ለጥማችን አለመድረሱም የዘወትር ሕመማችን ነበር። አሁን ግን ያ ዘመን ታሪክ ሆኗል።

ዓባይ ተገድቧል፤ ፍሬም መስጠት ጀምሯል። የዚህ ሒደት ደግሞ ጂጂ በኪነ-ጥበብ ሥራዋ ተንብያዋለች ቢባል ማጋነን አይሆንም።

አርቲስቷ በአንድ ወቅት ለአዲስ ዓመት የሙዚቃ ኮንሰርት ለማቅረብ ከአሜርካ ወደ አዲስ አበባ በመጣች ጊዜ የኢቢሲው ጋዜጠኛ ኤሊያስ አማን ቃለ መጠይቅ አድርጎላት ነበር።

ጂጂ በዓባይ የጥበብ ሥራዋ ግጥሙን ተጠንቅቃ እንደሠራችው የሚናገረው ጋዜጠኛ ኤሊያስ አማን፣

“ብነካህ ተነኩ አንቀጠቀጣቸው፤
መሆንህን ሳላውቅ ሥጋ እና ደማቸው’’

በሚለው የዘፈኗ ስንኝ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ መልኩ የዚያኛውን ወገን የፍርሃት ስሜት እና ፍላጎት መግለጧን ይናገራል።

አንድ ቀን ኢትዮጵያውያን በጋራ ክንዳቸውን አስተባብረው በአንድነት በመነሣት ዓባይን እንደሚነኩት እና እነርሱንም አንደሚያንቀጠቅጣቸው ጂጂ በዜማ ገልጸዋለች።

ደራሲ እና ጋዜጠኛ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ባለሙያው ስለአባት ማናዬ በተለይም በዓባይ ዙሪያ ምርምር በማድረግ ጽሑፉን ለአንባቢያን አበርክቷል።

ስለአባት ማናዬ ስለ አርቲስቷ የዓባይ ሥራ የገለጸችበትን መንገድ ሲያብራራ የዘፈኑ ጉልበት፣ ውበቱ፣ ኃያልነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓባይ ላይ ያለውን ቁጭት እና ስሜት፣ ሕመሙን የሚተነፍስበት ዜማ እንደያዘ ይናገራል።

“ዓባይ የወንዝ ውኃ አትሁን እንደ ሰው
ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብንለው
አንተ ወራጅ ውኃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጠኻል ከግብጾች ከተማ?"… ስትል በዜማዋ ወንዙን ጠይቃ "ዓባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ" ብላ ትዘጋዋለች።

ሙዚቀኛዋ ኢትዮጵያ ወንዙ ላይ ግድብ ገንብታ ማልማት ስትጀምር ከታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት “ተራብን፣ ተጠማን” የሚለው ድምፅ እንደሚሰማ ቀድማ በመረዳት ዛሬን የነገረችበት መንገድ ጥበብ የተሞላበት መሆኑን የገለጸው ስለአባት ማናዬ፣ ዓባይ የበረሃው ሲሳይ ለሁሉም የሚበቃ የተፈጥሮ ሃብት መሆኑን ይናገራል።

የሕዳሴው ግድብ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ፣ “አስዋን ግድብ ጎደለብን፣ የግብርና መሬታችን እየደረቀብን ነው” የሚለው የግብጽ ምሁራን ባዶ ጩኸትን ያጋለጡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት፣ አስዋን ግድብ በታሪክ አይተውት የማያውቁትን ውኃ ይዞ መገኘቱን ስለ አባት ይናገራል።

“በሰው ሰውኛ ሁሉ ነገር ያረጃል፤ ነገር ግን ዓባይ አያረጅም” የሚለው ስለአባት ማናዬ

“የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና’’

የሚለው የዘፈን ግጥም ላይ የዓባይን ውበት የገለጸችበትን መንገድ በአፍሪካ የወንዞች ታሪክ ዓባይ ሁልጊዜ እያበበ እና ሙሽራ እየሆነ የሚሄድ ወንዝ መሆኑን ይገልጻል።

ጂጂ በዘፈኗ ውስጥ የወንዙን ውበት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህሪ፣ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን አይለቅም” የሚለውን አገላለጽ በወንዙ ሰውኛ ዘይቤ ነግራናለች ይላል ስለአባት።

ዓባይ መነሻውን ኢትዮጵያ አድርጎ የጎረቤት ሀገራትን ጉሮሮ ሲያረሰርስ ኗሯል። ወንዙ የብዙ ሀገራት ጥቅም የተሳሰረበት በመሆኑም የእርሱ መነካት የሚያስነሣው ፖለቲካዊ ትኩሳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ስለ ዓባይ ውበት እና ጉልበት በኪነ-ጥበብ ብዙ ተብሎለታል። እጅጋየሁ ሽባበው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር በሚችል መልኩ ከፍ ባለ የጥበብ ሥራዋ ዓባይን የገለጸችበት መንገድ በኢትዮጵያዊያን ልብ እንድትነግሥ አድርጓታል።

ኢትዮጵያዊያን ከዓባይ ወንዝ ጋር ያላቸውን ተጋምዶ እና ፍቅር ለመግለጽ ቃላት ሲያጥራቸው ወደ ጂጂ ዘፈን ጎራ ማለታቸው አይቀርም ይባላል።

የእጅጋየሁን ዓባይ ዘፈን የቅኔውን ትርጉም ለመግለጽ እና ለማብራራት ቃላት ሲያጥሩ እንዲሁ ሙዚቃውን ከፍቶ መመሰጡን የሚመርጡም በርካቶች ናቸው።

በመሐመድ ፊጣሞ

#EBC #ebcdostream #GERD #gigi


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top