ስለ ነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር ምን ያህል ያውቃሉ?

8 Hrs Ago 194
ስለ ነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር ምን ያህል ያውቃሉ?

በአንዲት እናት ማህጸን ውስጥ ፅንስ ከተፈጠረ በኋላ ሙሉ የሰውነት ክፍሎች መፈጠር ይጀመራሉ።

በዚህ ሂደት ከልብ ቀጥሎ ወዲያው መፈጠር የሚጀምረው የነርቭ ሥርዓት ሲሆን፤ የነርቭ ሥርዓት የሚፈጠረው ደግሞ እርግዝና ከተፈጠረ ከሦስተኛው ሳምንት በኋላ ነው።

በዚህ ጊዜ አንጎልን፣ ህብለ ሰረሰርንና ነርቮች የሚሠሩት ክፍሎች ላይ ክፍተት ሲፈጠር የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር /spinal bifida/ ሊከሰት ይችላል ፡፡

የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር ብዙ የሰውነት ክፍሎችን ሥርዓት ያዛባል።

የዳሌ መገጣጠሚያ ችግሮችና የእግር መቆልመም ያጋጥማል። በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ህፃናት በእግራቸው መቆም እንዲሁም መራመድ ሊሳናቸውም ይችላል።

የሽንት መቆጣጠር ችግር ያጋጥማል። በጭንቅላት ውስጥ ውኃ መጠራቀም ይኖራል። ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫናም ያስከትላል።

ለነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር እንደ ዋና መንስኤ ሆኖ የተቀመጠውና በሳይንስም የተረጋገጠው የፎሊክ አሲድ እጥረት ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በፅንስ ወቅት ለካንሰርና ለሚጥል በሽታ የሚወሰዱ መድኃኒቶች በተዘዋዋሪ በፎሊክ አሲድ ላይ ጣልቃ ስለሚገቡ ለነርቭ ዘንግ አፈጣጠር  ችግር  ሊያጋልጡ ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ  የስኳር ህመምም ለነርቭ ዘንግ  አፈጣጠር ችግር  ሊያጋልጥ የሚችልበት እድል አለ።

ከእርግዝና በፊት የሚከሰት ውፍረት፣ የዘረ መል ችግሮች፣ ከዚህ በፊት በቤተሰብ ውስጥ የነበሩ እርግዝና ላይ ችግሮች  ከነበረ የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር  የመከሰት  ዕድሉን  ከፍ ያደርገዋል።

ከዚህ ውጭ ወጣት በሆኑና እርግዝና የመጀመሪያቸው በሆኑ ሴቶች ላይም ይህ ችግር ሲያጋጥም ይታያል።

ስለ ፎሊክ አስድ ጠቀሜታዎች የሥነ ምግብ  ባለሙያው አላዛር ኪሩቤል ከኢቲቪ ጤናዎ በቤትዎ መሰዳዶ ጋር  ባደረጉት ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከቫይታሚን ቢ ኮምፕሌክስ ውስጥ ፎሊክ አሲድ ‹‹ቢ ናይን›› አንዱ መሆኑም  ገልጸው፤ ይህ ንጥረ ነገር አስፈላጊ ነው የተባለበትም ዋነኛው ምክንያት በሰውነት ውስጥ ስለማይመረት መሆኑን ተናግረዋል።

በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት በልጇላይ የሚከሰቱ የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር ችግር እና የጭንቅላት ውስጥ ፈሳሽ ከመጠን በላይ ክምችት ችግሮችን ለመከላከል በሕክምና ባላሙያዎች የሚሰጡ የፎሊክ አሲድ እንክብሎችን እንድትወስድ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ይህን ንጥረ ነገር ከምግብ ምንጭ ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል።

አብዛኛው እናቶች እርግዝና መከሰቱን  የሚያውቁት ከሁለትና ሶስት ወር በኋላ ነው። የነርቭ ዘንግ  ደግሞ የሚፈጠረው ፅንስ ከተፈጠረ በሁለተኛው ሳምንት ነው። ያ ማለት እርግዝና ከተከሰተ ከሁለትና ሶስት ወር በኋላ እናቶች የፎሊክ አሲድ መውሰድ ቢጀምሩ እንኳን የነርቭ ዘንግ  አፈጣጠር ችግርን ለማስቀረት ይቸገራሉ ማለት ነው፡፡

ፅንሱ በሆድ ውስጥ እንዳለ በአልትራሳውንድ በሚደረግ ምርመራ የነርቭ ዘንግ  አፈጣጠር ችግርን እንዳለ መለየት ይቻላል። በተለይ በሁለተኛው የእርግዝና ክፍል ላይ ማለትም ከአስራ ስድስት እስከ ሀያ ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንዳለና እንደሌለ ማረጋገጥ አያዳግትም።

ህፃናት ከተወለዱ በኋላ የነርቭ ዘንግ  አፈጣጠር  ችግር ሲኖርባቸው በአከርካሪ አጥንታቸው ላይ ክፍተት ወይም ዕባጭ ነገር ይታይባቸዋል  በተጨማሪም የጭንቅላት መጠናቸውም ይገዝፋል።

የነርቭ ዘንግ አፈጣጠር  ችግር ከተከሰተ በኋላ ሊታከም ይችላል። ሕክምናው የሚጀምረውም በፅንሱ ላይ የነርቭ ዘንግ  አፈጣጠር  ችግር መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

የነርቭ ዘንግ ክፍተት እና የጭንቅላት ውስጥ ፈሳሽ ከመጠን በላይ ክምችት በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሺዎች በሚቆጠሩ ሕፃናት ላይ የሚከሰት የአፈጣጠር  ችግር መሆኑ ይገለጻል።

በኃይማኖት ከበደ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top