ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሯ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ጠንካራ መልዕክት ለዓለም ማስተላለፏን የናይጄሪያ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አይዛክ ሳላኮ ገለጹ።
በዱባይ እየተካሔደ በሚገኘው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ተሞክሮዎቿን የምታካፍልበት የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) በሀገራት መሪዎች እና በጉባዔው ተሳታፊዎች እየተጎበኘ ነው።
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የጎበኙት የናይጄሪያ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አይዛክ ሳላኮ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ መልዕክት ለዓለም ማህበረሰብ አስተላልፋለች።
የተዘጋጀው ፓቪሊዮን የዓለም ሕዝብ ፊቱን ወደ ተፈጥሮ እንዲመልስ የሚጠይቅ ወሳኝ መልዕክት የተላለፈበት መሆኑንም አስረድተዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች የምትገኘውን ዓለም ከችግሩ ለማዳን ተፈጥሮን በተፈጥሮ ለማከም እየተደረገ ያለው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ተፈጥሮን መንከባከብ በሌላ በኩል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚኖረው አስተዋጽዖም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።