ለውጥ የመጣለት እና የታደገው ፕሮጀክት

27 Days Ago
ለውጥ የመጣለት እና የታደገው ፕሮጀክት

ኢትዮጵያ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቧ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኘ አይደለም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ መቶ በመቶ የሚሆነው የግብፅ ሕዝብ መብራት እያገኘ ነው፡፡ ይህ ንጽጽር ሲታይ ኢትዮጵያ ሀብቷን ተጠቅማ እንዳትለማ ለዘመናት የተደረገባትን ጫና ማሳያ ነው፡፡

ይህን ታሪክ ለመቀየር ታላቁን ህዳሴ ግድብ መገንባት ስትጀምር ደግሞ ጫናው ከውስጥም ከውጭም እየተጠናከረ፣ ወከባ እያየለ መጣ፡፡ የግድቡ ግንደባታ በተጀመረ 6ኛ ዓመቱ መጋቢት 2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ መጣ፡፡

የለውጡ መሪዎች የቅድሚያ ትኩረታቸው ካደረጉአቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሆነ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የግድቡን የሥራ ሂደት፣ በሥራ ሂደቱ ያጋጠሙ እክሎችን፣ ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ በጥልቀት እንዲጠና አቅጣጫ በመስጠት ጉዳዩን በቀጥታ መከታተል ጀመሩ፡፡ 

የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ)

በወቅቱ የሲቪል የግንባታ ሥራውን የያዘው ሳሊኒ የግንባታውን ከ80 በመቶ በላይ ማድረሱን አረጋገጠ፡፡ የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራውን ይዞ የነበረው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪኒግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሥራውን 25 በመቶ ማጠናቀቁን ሪፖርት አቀረበ፡፡

በወቅቱ በተደረገው ምርመራ የኤሌክትሮሜካኒካሉ ሥራ ግን ከ2 በመቶ የበለጠው እንኳን በትክክል አልተሠራም ነበር፡፡ ውሃ የሚተኛበትን መሬት ምንጣሮ ሥራን ጨምሮ የወሰደው ሜቴክ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጌያለሁ ቢልም ምንም ባለመሠራቱ ግድቡ ውሃ መያዝ ሳይችል ወደ ሰባተኛ ዓመቱ ተሸጋገረ፡፡ በዚህም ምክንያት በ80 ቢሊዮን ብር ወጪ በ5 ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ የመጀመሪያውን የውኃ ሙሌት እንኳን ሳያከናውን 6 ዓመታት አለፉት፡

የግምገማው ውጤት ከታወቀ በኋላ ምን እርምጃ ተወሰደ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጊዜ ወስደው ፕሮጀክቱን እንዲገመገም ካደረጉ እና ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ ቀጣይ አፈጻጸሙን በቀጥታ መከታተል ጀመሩ፡፡ የኤሌክትሮሜካኒካሉ ሥራ የሚገባውን ያክል ባለመሄዱ ግድቡ ውሃ መያዝ እንደማይችል በመታወቁ ሥራው ከመሰረቱ ተስተካክሎ እንዲሠራ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ ሥራው ቀድሞውን ምንም ልምድ ሳይኖረው በጉልበት ከገባበት የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተወስዶ ዓለም አቀፍ ተቋራጮች በጨረታ ተወዳድረው እንዲገቡበት ተደረገ፡፡ ክትትሉም በቀጥታ ለሚመለከተው የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ተሰጥቶ ሥራው እንዲቀጥል ተደረገ፡፡

ግድቡን የማዳን ውሳኔ የገለጠው ምስጢር

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራርነት ችግሮቹ ታርመው ወደ ሥራ ሲገባ ቀድሞን የግድቡን ሥራ በሥርዓት ከመምራት ይልቅ በግብተኛ ውሳኔ ወደ ውድቀት ዋዜማ ላይ አድርሰውት የነበሩ ወገኖች "ግድቡ ተሸጧል" የሚል ውዥንብር መንዛት ጀመሩ፡፡ በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ ቀዝቀዝ ብላ የነበረችው ግብፅ ዘመቻዋን በተለየ ሁኔታ አጣናክራ ቀጠለች፡፡ እነዚህ ግድቡ ተሽጧል ሲሉ የነበሩ ወገኖች ከግብፅ እና ጀሌዎቿ በሚሰጣቸው ማበረታቻ ሀገሪቱን ሰላም መንሳታቸውን ቀጠሉ፡፡

የአሜሪካ ተፅዕኖ እና የፀጥታው ምክር ቤት

አሜሪካ በድርድሩ ላይ ትገኝ የሚለውን የግብፅ ጥያቄ ኢትዮጵያ በታዛቢነት እንዲሆን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣ ተቀበለች፡፡ በታዛቢነት የገባችው አሜሪካ ግን በጉዳዩ ላይ መወሰን አለብኝ ብላ ተነሳች፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅ በምትፈልገው መንገድ ካልተስማማች እርዳታ ከመከልከል ጀምሮ ሌሎች እርምጃዎችን እንደምትወስድ ዛተች፡፡ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም የግብፁን ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲን ከጎናቸው አስቀምጠው፣ "ኢትዮጵያ ግብፅ በምትለው መንገድ ካልተስማማች አደገኛ ነገር ይፈጠራል፤ ግብፅ ግድቡን ታፈነዳለች" በማለት አስፈራሩ፡፡

በግብፅ ወትዋችነት እና በአሜሪካ ገፊነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤትም ጉዳዩን ለመመልከት ስብሰባ ጠራ፡፡ ይህም በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ታሪክ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት የሄደ የመጀመሪያው ጉዳይ ያደርገዋል፡፡ የዓምን በተለይም አሜሪካ መሩን የምዕራብ ዓለም ኢ-ፍተሃዊነት በታሪክ የተጋለጠበት ክስተትም ሆኖ አለፈ፡፡

"ግድቡ የኔ ነው!" /"It is My Dam!"

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ በታሪኳ የማንንም ፍትሃዊ ፍላጎት ተጋፍታ አታውቅም፡፡ ሌሎች አልፈው ሲመጡባት ግን ሕዝቧን አስተባብራ ጥቅሟን ስታስከብር ኖራለች፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይም የታየው ይህ ነው፡፡ ዓለም የሷን የውኃ ሀብት እንዳትጠቀም በሩን ሲዘጋባት እጇን አጣጥፋ እንዳልተቀመጠች ሁሉ ግንባታውን እንዳትቀጥል ጫናውን ሲበረታባት ሕዝቧን አስተባብራ መክታለች፡፡ ለዚህም ትልቁ የመታገያ ቃል እና ማሰባሰቢያ "ግድቡ የኔ ነው!" (It is My Dam!) የሚለው ንቅናቄ አንዱ ነው፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ እና በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ሲደረጉ የነበሩትን የእጅ መጠምዘዝ ሙከራዎችን በጋራ ሆነው መክተዋል፡፡ በተለይም ዓረብኛ ተናጋሪ የኢትዮጵያ ልጆች ያለምንም ክፍያ የግብፅን ፕሮፓጋንዳ ለመመከት ያደረጉት ተጋድሎ በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው፡፡

ግድቡ የኢትዮጵያውያን የወል ፕሮጀክት ስለሆነም ሁሉንም ፈተናዎች ተቋቁሞ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት አሃዱ ብሎ ጀምሮ በ2015 ዓ.ም አራተኛውን እና የመጨረሻውን ሙሌት አጠናቋል፡፡ ሁለት ተርባይኖችም ወደ አገልግሎት ገብተው 1 ሺህ 500 ሜጋ ዋት ማመንጨት ጀምረዋል፡፡ የማመንጨት አቅሙን ወደ 2 ሺህ ሜጋ ዋታ የሚያሳድገው ሦስተኛው ተርባይንም በቅርቡ እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን፣ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ በሚቀጥሉት ሰባት ወራት እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

በቁርጥ ቀን የተገኙ ጀግኖች

ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሁሉም በየራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከህይወት መስዋዕትነት እስከ ጉልበት እና ገንዘብ እንዲሁም በፀሎት ጭምር ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ስኬት የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ አቶ ኪሮስ አስፋው ታሪክም ከነዚሁ በቁርጥ ቀን ከተገኙ የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ናቸው፡፡ የ56 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ ኪሮስ ትውልድና ነዋሪነታቸው በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በአቢይ አዲ ከተማ ነው፡፡ ለዓባይ ግድብ ግንባታ ለሦስት ዓመት በተከታታይ ቦንድ ለመግዛት ወስነው ቃላቸውን በተግባር የተረጎሙ ናቸው፡፡ ግድቡን ካዩ በኋላ ግን ግንባታው ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም እስከ 2013 ዓ.ም በተከታታይ ለ10 ዓመታት ቦንድ መግዛታቸውን ቀጥለዋል። በዚህም በተከታታይ ያለማቋረጥ ለ102 ወራት ቦንድ ገዝተዋል። በዚህም የ180 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተው ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈዋል፡፡

አሁን የግድቡ የሲቪል ሥራው ግንባታ 99 በመቶ ተጠናቋል፡፡ 107 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት የሚያስፈልገው ዋናው የግድቡ ክፍል አንድ በመቶ ብቻ ሙሌት ብቻ ይቀረዋል። የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል በተለይም የተርባይን እና ጄኔሬተር ተከላ ሥራው 78 በመቶ ተጠናቋል። የግድብ የውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳዎች ግንባታ ከ85 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ድምር የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 95 በመቶ ደርሷል።

  • 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይዟል፡፡
  • ግድቡ እስካሁን የፈጀው ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡
  • በመጪዎቹ ሳምንታት 5 ተርባይኖች ሥራ እንደሚጀምሩ የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ገልጿል።
  • በአሁኑ ሰዓትም ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል እየተሸጠ ሲሆን፣ ለታንዛኒያ እና ለደቡብ አፍሪካ ለመሸጥ ታቅዶ ንግግር ተጀምሯል፡፡
  • አጠቃላይ ሥራዎቹ በ2017 ዓ.ም በማጠናቀቅ የመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነውን የዓባይ ግድብ ከፍጻሜው ለማድረስ አስፈላጊው ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

ተስፋ አስቆራጭ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለስኬት የበቃው የፕሮጀክቱ ግንባታ የኢትዮጵያ ተቋማት የጥራት ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ይህም ለአመራሩም ሆነ ለሠራተኛው ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ድርብ ሽልማት ነው፡፡

ግድቡ ሀገር የትውልዶች ሥራ ድምር ውጤት መሆኗን ምስክር የሆነ ታላቅ ሀውልት ነው፡፡ አንድነት ተአምር የሚሠራበት ኃይል መሆኑን ምስክር የሆነ ‘የኢትዮጵያውያን የላብ ማኅተም’ ነው፡፡ ስንተባበር ሁሉንም የጎደፉ ታሪኮቻችንን መቀየር እንደምንችል በተግባር ያሳየንበት ትልቅ ማስተማሪያም ነው፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top