በመዲናዋ በመከናወን ላይ ያለው የኮሪደር ልማት የተዋቀረ የከተማ ልማት እንዲኖር ያስችላል - ተባባሪ ፕሮፌሰር አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ

20 Days Ago
በመዲናዋ በመከናወን ላይ ያለው የኮሪደር ልማት የተዋቀረ የከተማ ልማት እንዲኖር ያስችላል - ተባባሪ ፕሮፌሰር አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀከት ከተማዋን ሳቢ እና ማራኪ እንዲሁም ለቱሪስት ምቹ በማድረግ አዲስ እይታን እንደሚፈጥር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማ እና የአርክቴክት ቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፋሲል ጊዮርጊስ ገለፁ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር አርቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ብስክሌትና ሌሎች የመዝናኛና የእግር ጉዞ እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የሚይዝ በመሆኑ የከተማ ደረጃን ለማሻሻል ሚናው የላቀ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡    

በኮሪደር ልማት ስራው ህንጻዎች በውበት ከተገነቡ ተስማሚ የሆነ የከተማ እይታን ያመጣል የሚሉት ኃላፊው፤ ከተሞችም ይበልጥ የተዋቀረ የከተማ ልማት እንዲኖራቸው እና ሳቢ እንዲሆኑ እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡

አንድ ከተማ ለነዋሪዎች ምቹ ነው የሚባለው የተስተካከለ የመንቀሳቀሻ መንገዶች ሲሟሉ ጭምር እንደሆነም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ከሌሎች ሀገራት ከተሞች ልዩ የሚያደርጋት አፍሪካዊ ከተማ በመሆኗ ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አርቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ፤ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ  ገዢዎቻቸው ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ አዲስ አበባ ግን የተቆረቆረችው ከዚህ በተለየ ሁኔታ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

ሀገራት የራሳቸው የከተማ አገነባብ ስላላቸው የኮሪደር ልማቱ ታሪካዊ ቦታዎች እንዲሁም ቅርሶችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንደሚገባውም አርቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡

በጣም ያረጁ እና ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ ቦታዎችን ሳቢ ለማድረግ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት  የሚከናወኑ ስራዎችም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

በሜሮን ንብረት 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top