ውል ማስፈፀም እና ቀብድ

1 Mon Ago 724
ውል ማስፈፀም እና ቀብድ

ውል ማስፈፀም እና ቀብድ

ውሎች ሁሉ ወዲያውኑ ተፈፃሚ ሊሆኑ አይችሉም። በተለያዩ ምክንያቶች ተዋዋዮች ከስምምነት ላይ ቢደርሱም የውሉን ሙሉ ክፍያ ለመክፈል ወይም በውሉ ግዴታ የገባው ወገን ግዴታውን ለመወጣት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ለማሟላት የተወሰነ ጊዜ ሊፈልግ ይችላል። በዚህ ጊዜ መሀል ተዋዋዮች ሀሳባቸውን ሳይቀይሩ ዋናውን ውል እንዲፈፅሙ ከሚያስተማምኑ መንገዶች አንዱ ቀብድ ነው።

ቀብድ ከውል አፈፃፀም ጋር ያለውን ግኙነት እና ስለ ውጤቱ ሕጉ ምን እንደሚል ለማየት፣ ውልን አለመፈፀም ማለት ምን እንደሆነ እና በሕግ የተቀመጡ የውል ማስፈፀሚያ መንገዶችን፣ እንዲሁም ቀብድ በተዋዋዮች የውል መብት እና ግዴታ ላይ የሚኖረውን ውጤት እንመልከት።

 ውልን አለመፈፀም

የፍትሐ ብሔር ሕጉን እየተመለከትን ቁጥር 1731(1) ላይ ስንደርስ ውል በተዋዋዮች መሀከል ሕግ ነው ይለናል። ተዋዋዮች በመሀላቸው ላለው ግንኙነት ተፈፃሚ እንዲሆን በነፃ ፍላጎታቸው የሚፈጥሩት መብት እና ግዴታ ነውና ውሉ እና ሕጉ ላይ የተቀመጡትን የተዋዋዮች መብቶች እና ግዴታዎች መፈፀም አለባቸው፡፡ ውሉ አልተፈፀመም የሚባለው ተዋዋዮቹ በውል ስምምነታቸው እና በሕጉ መሰረት ግዴታቸውን ሳይወጡ ሲቀሩ ነው፡፡

ተዋዋዮች ውል የሚገቡት በተስማሙባቸው ነገሮች ላይ የልብ ልብ ተሰምቷቸው እንዲተማመኑበት ነው፡፡ ይህን መተማመን የሚፈጥረው ደግሞ ውልን የሚያስፈፅመው ሕግ ነው። በውሉ እና በዚህ ሕግ ላይ ተመስርተው ፍ/ቤቶች በሚሰጡት ፍርድ ነው ውል የሚፈፀመው፡፡ ስለዚህ ሕጉ በምን መልኩ ውልን ያስፈፅማል ወደ ሚለው ጉዳይ እንለፍ፡፡

 ውልን በግድ ማስፈፀም

የውል ግዴታውን ያልፈፀመ ተዋዋይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1776 መሰረት ለሌላው ተዋዋይ የተለየ ጥቅም የሚሰጠው እና በፈፃሚው ነፃነት ላይ ምንም መሰናክል ሳይፈጥር መፈፀም የሚችል ግዴታ ሲሆን በሕግ ተገዶ እራሱ እንዲፈፅም ይደረጋል፡፡

ለምሳሌ በአንድ የሙዚቃ አቀናባሪ እና በአንድ ድምፃዊ መሀከል ሙዚቃ ለማቀናበር የተደረገ የውል ግዴታን እንይ። አቀናባሪው እና ድምፃዊው ውሉን ከገቡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቀናባሪው ግልፅ ባልሆነ የራሱ ምክንያት ሙዚቃውን ሳያቀናብር ይቀራል። ድምፃዊው ከሙዚቃ አቀናባሪው ጋር ውሉን የገባው የአቀናባሪውን የታወቀ ልዩ የማቀናበር ችሎታን ዓይቶ ስለሆነ ወደ እርሱ የመጣው የማቀናበሩ ሥራ በራሱ ባቀናባሪው በመሠራቱ ላይ ልዩ ጥቅም አለው ሊባል ቢችልም አቀናባሪው ግን በፖሊስ ተገዶና በፍ/ቤት ታዞ የአቀናባሪውን ፍላጎትን እና መነሳሳትን የሚጠይቀውን የሙዚቃ ቅንብር ሥራ ሊሠራ ስለማይችል ሥራው ቢባልም ነፃነቱ ስለሚጣስ በግድ ፈፅም ሊባል አይችልም። 

ውልን በአማራጭ እንዲፈፀም ማስገደድ

ይህ ደግሞ ከላይ ባነሳነው መልኩ ተዋዋዩን እራሱን አስገድዶ ማስፈፀም ካልተቻለ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1777 መሰረት በፍ/ቤት ትዕዛዝ ውል ገብቶ ግዴታውን ባልፈፀመው ሰው ወጪ ግዴታው በሌላ መልኩ እንዲፈፅም ማድረግ ነው። ለምሳሌ ከላይ ባነሳነው ምሳሌ ላይ በአቀናባሪው የተጀመሩ ቅንብሮች ካሉ የሚያስከትሉትን ተጨማሪ ወጪ አቀናባሪው እንዲሸፍን በማድረግ ሌላ ባለሙያ እንዲያቀናብረው በማድረግ ውሉን ሳይፈፅም በቀረው ሰው ወጪ በአማራጭ ውሉን በሌላ አቀናባሪ በኩል ማስፈፀም ነው፡፡ 

ውሉን መሰረዝ

ውሉ ያልተፈፀመለት ሰው በፍ/ቤት በመክሰስ ወይም በግሉ ለተዋዋዩ በማሳወቅ ውሉ እንዲፈርስ እና ተዋዋዮች የውል ግንኙነታቸው እንዲያበቃ ማድረግ ይችላል። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1784 መሰረት ፍ/ቤቱ መሰረታዊ የውሉ ጉዳዮች ሊፈፅሙ እንዳልቻሉ ካመነ ውሉ እንዲፈርስ ያዛል፡፡ አንደኛው ወገን በግሉ ውሉን ከሚያፈርስባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ሌላኛው ተዋዋይ በማያሻማ ሁኔታ ውሉን እንደማይፈፅም ከገለፀ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ1784(1) ላይ ተጠቅሷል። ውሉ ከፈረሰ ተዋዋዮች በተቻለ መጠን ከውሉ በፊት ወደ ነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ። አንዱ ለሌላኛው የከፈለው ገንዘብ ወይም ያስረከበው ንብረት ካለም ለሌላኛው እንዲመልሱ ይደረጋል፡፡ 

የጉዳት ካሳ መጠየቅ

ከላይ ካነሳናቸው የውል ማስፈፀሚያ ድንጋጌዎች በተጨማሪ ወይም በአማራጭነት አንደኛው ተዋዋይ የውል ግዴታውን ባለመፈፀሙ ሌላኛው ተዋዋይ ላይ የደረሰበት ጉዳት ካለ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1790 መሰረት ‘‘እንደውሉ ቢፈፀም ኖሮ ላገኝ እችል የነበረውን ይሄን ያህል ጥቅም አሳጥተኸኛል ስለዚህ ካሳ ክፈለኝ’’ ብሎ ሌላኛውን ተዋዋይ መክሰስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከላይ ባነሳነው የአቀናባሪው እና የድምፃዊው ውል ላይ ለአቀናባሪው ሙዚቃውን እንዲያቀናብርለት የሰጠው ድምፃዊ  አልበሙን ለማስተዋወቅ መቶ ሺ ብር አውጥቶ ነበር ብንልና ማስታወቂያው ምርጥ አቀናባሪ በሆነው በእከሌ የሚቀናበር በመሆኑ ከነበረ  አቀናባሪው ሙዚቃውን አላቀናብርም በማለቱ የማስታዉቂያው መቶ ሺ ብር ቀለጠ ማለት ነው። ስለዚህ ይህንን እና ሌሎች ወጪዎችን አቀናባሪው እንዲከፍለው ተዋዋዩ መጠየቅ ይችላል፡፡

ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል

በመርህ ደረጃ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1791(1) ጥፋትም ባይኖርበት የውል ግዴታውን ባለመፈፀሙ ሌላኛው ተዋዋይ ላይ ጉዳት ያደረሰ ተዋዋይ ኪሳራውን የመሸፈን ግዴታ እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ሆኖም ኪሳራ የሚጠይቀው ተዋዋይ ካሳ ማግኘት የሚችለው ውሉን ሳይፈፅም የቀረውን ሰው ጥፋት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1796 መሰረት ሲያስረዳ ነው፡፡

ውሉን ያልፈፀመው ሰው ካሳ ከመክፈል የሚድነው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1791(2) መሰረት ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ግዴታውን ሳይፈፅም ከቀረ ነው። ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል የሚባለው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1792 መሰረት ያልታሰበ እና ድንገተኛ ደራሽ ሰው ሰራሽ ወይም የተፈጥሮ ክስተት ሆኖ ተዋዋዩን ግዴታውን እንዳይፈፅም ፍፁም መሰናክል ከሆነበት ነው። ግዴታውን ያልፈፀመው ተዋዋይ በአዕምሮ ግምት ቀደም ብሎ ሊያስብበት የሚችለው የታወቀ ድንገተኛ ነገር ከባድ ወጪ የሚያስከትልበት ቢሆንም ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ተደርጎ አይቆጠርም፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1793 ስር የውል ግዴታውን ያልፈፀመ ተዋዋይን ላደረሰው ጉዳት ካሳ ከመክፈል ሊያድኑት የሚችሉት ከአቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች ተዝርዝረዋል። ውሉን ያልፈፀመው ሰው ኃላፊ የማይሆንባቸው ያልታሰቡና በሌላ ሰው ላይ የሚመጡ ድንገተኛ ነገሮች ውሉ እንዳይፈፀም በመንግስት የሚደረግ ክልከላ  እንደ መሬት መንቀጥቀጥ እና መብረቅ የመሰሉ የተፈጥሮ መቅሰፍቶች፣ ጦርነቶች እና ውሉን ያልፈፀመው ሰው መሞት ወይም የሚደርስበት ከባድ አደጋ ወይም ፅኑ ህመም ናቸው። 

የቀብድ ጉዳይ

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1883 መሰረት ቀብድ ማለት ከአጠቃላይ የውል ሕግ ድንጋጌዎች በተጨማሪ ተዋዋዮች ውላቸውን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ ወይም ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ስምምነት አንዱ ለሌላኛው አስቀድሞ የሚሰጠው የተወሰነ የገንዘብ መጠን ነው፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1884 መሰረት የቀብድ ገንዘብ የተቀበለ ተዋዋይ የተቀበለውን ቀብድ ሥራው ሲጠናቀቅ ለሰጪው ይመልሳል ወይም ከሚከፈለው አጠቃላይ የስራው ዋጋ ላይ ተቀናሽ ተደርጎ ይታሰብለታል፡፡

ሆኖም ቀብድ ተቀባይ ውሉን ሳይፈፅም በመቅረቱ በውላቸው ላይ በሌላ መልኩ ካልተስማሙ በስተቀር ቀብድ ሰጪው በራሱ ተነሳሽነት ውሉን ማፍረስ ከፈለገ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1885(1) እንደሚያዘው የሰጠውን ቀብድ ለተቀባዩ ትቶ ውሉን ማፍረስ ይችላሉ፡፡

ነገር ግን ውሉን ያፈረሰው ቀብድ ተቀባዩ ከሆነ በውላቸው ውስጥ ሌላ ስምምነት ከሌለ በስተቀር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1885(2) መሰረት የተቀበለውን ቀብድ እጥፍ ከፍሎ ነው ውሉን ማፍረስ የሚችለው፡፡

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top