ዘመናትን ያስቆጠረ ተቀናቃኝነት ወደ ፍልሚያ ሜዳ ይሄድ ይሆን?

14 Days Ago
ዘመናትን ያስቆጠረ ተቀናቃኝነት ወደ ፍልሚያ ሜዳ ይሄድ ይሆን?

በርካታ ጦርነቶችን አድርገዋል፤ አንዳቸው ለአንዳቸው መጥፋት እና መውደም ሳይታክቱ እየሰሩ አሁንም ይተጋሉ።

ሁለቱም ሀገራት መንግሥታቶቻቸው ሲቀያየሩ ያለፈው የጀመረውን የማዳከም እና የማጥቃት ተግባር ለማስቀጥል ይጨባበጣሉ።

የታሪክ ዳራቸው ብዙ ዓመታትን ይህ ነው የማይባል እና ከመዋደድ አይሉት ከመጠላላት ሊፈርጁት የሚከብድ ከጊዜ በኋላ ግን የለየ ግንኙነታቸውን እንካቹ ይለናል።

ፊት ለፊት አውጀው ጦርነትን ባይገጥሙም ቀዝቀዝ ባለው መንገድ እና በተዘዋዋሪ ጦርነት ላይ ናቸው ኢራን እና እስራኤል።

ኢራን በሶሪያ በሚገኘው ቆንሲላዋ ላይ ለደረሰው ጥቃት አጸፋ ነው ያለችውን እርምጃ እስራኤል ላይ ወስዳለች። እስራኤል ደግሞ ለተደረገባት ትንኮሳ ተመጣጠኝ እርምጃ እንደምትወሰድ አስታውቃለች። የእስራኤል የጦር ካቢኔ ኢራን ላይ አፃፋዊ እርምጃ ለመውሰድ የመከረ ሲሆን መቼ እና እንዴት እርምጃው ይወሰድ የሚለው ላይ ግን ወሳኔ ላይ አልደረሰም። እስራኤል በቀጣይ ጊዜያት አጸፋ እርምጃ መውሰዷ እንደማይቀር ግን አንድ የካቢኔው አባል መናገራቸውን ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ፍንጭ ሰጥቷል።

ለመሆኑ የእነዚህ ሁለት ሀገራት ባላንጣነት ከምን የመነጨ ነው? ኢራን በእስራኤል ላይ ላደረሰችው ጥቃት እስራኤል የአጸፋ እርምጃ ወስዳ ቀውሱ ወደ ቀጠናው ይስፋፋ ይሆን? ቀጥለን እንመለከታለን አብራችሁን ቆዩ፡፡

የእስራኤል እና ኢራን የግንኙነት ታሪክ የሚጀምረው ከጥንት ባቢሎን ዘመን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ዋቢ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የኢሳይያስ፣ የዳንኤል፣ የዕዝራ፣ የነህምያ እና ሌሎች የእስራኤል ነቢያት ዜና መዋዕሎች በግዞት በፋርስ ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ስላጋጠሟቸው ችግሮች ይጠቅሳሉ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው ክፍለ ዘመን የፋርስ ንጉሥ ታላቁ ቂሮስ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሳቸውን መልሰው እንዲሠሩ እንደፈቀደላቸውም ይነገራል። በዚህ ወቅት በፋርስ ውስጥ በደንብ የተቋቋመ እና ተደማጭነት ያለው የአይሁድ ማኅበረሰብ ነበር። አይሁዶች በቀድሞው ባቢሎን በዛሬዋ ኢራን ውስጥ ከ2 ሺህ 700 ዓመታት በላይ ኖረዋል።

ትንሽ ወደ ቅርቡ መጣ እንበል እስቲ።

በአውሮፓውያኑ 1970 israel-iranian pipeline በመባል በሚታወቀው መስመር በጋራ በመሆን በእስራኤል በኩል ለአውሮፓ ነዳጅ ይልኩ ነበር። ከ1980-1988 ለተደረገው የኢራን እና ኢራቅ ጦርነት እስራኤል የጦር መሳሪያ እና የጦር መሪዎችን በመስጠት ስታግዛት የነበር ሲሆን በተለይም የኢራቅ የኒኩለር ማመንጫን እንድታደባየው በማድረጉ ረገድ የቀኝ እጇ ነበረች። በ1982 የእስራኤል ሊባኖስን መውረር ተከትሎ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት ከሊባኖስ እንዲነሳ ምክንያት ሆነው፡፡ ከዚህ በኋላ በአንድ መሰናዶ ልንዳስሳቸው እና ልናስረዳቸው የማንችላቸው ብዙ የረቀቁ እና የተጠኑ ፍጭቶችን አሳልፈው ይህን መሰል መልካም ግንኙነታቸው በነበር የቀረ ሆነ፡፡

ከፍተኛ የአይሁድ መገኛ የሆነችውን የእስራኤልን መኖር የምትቃወመው ኢራን ያላት መጥፎ እይታ ጥጉ እምነት የሚመስላቸው ብዙዎች ቢሆንም ጉዳዩ ሌላ መልክ ያለው ነው: መካከለኛው ምስራቅ ላይ የኢራን እና የእስራኤል የጦር አቅም እጅጉኑ የጠነከረ በመሆኑ በአካባቢው የሃያልነትን ቦታ መቆናጠጥ እና እስራኤል ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነትም በቁራኛ መመልከትንም ይጨምራል፡፡ እስቲ ነገሮችን በጥልቀት ለመመልከት እንሞክር? በ1948 እስራኤል  እራስ ገዝነቷን ስታውጅ  ኢራን እውቅናን የሰጠች የመጀመሪዋ የብዙ  ሙስሊሙች መገኛ  ሀገር ናት፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ዘመናዊ ግንኙነት ደግሞ በአራት ዐበይት አንጓዎች የተከፈለ ነው፡፡ እ.አ.አ ከ1947 እስከ 1953 ድረስ ያለው ጊዜ ውሉ ያልለየ አሻሚ ዘመን፣ ከ1953 እስከ 1979 በፓህላቪ ሥርወ መንግሥት ዘመን የወዳጅነት ዘመን፣ ከኢራን አብዮት በኋላ ያለው ከ1979 እስከ 1990 ግንኙነታቸው እየተበላሸ የመጣበት ዘመን እና የ1991 የባሕር ሰላጤው ጦርነት ካበቃበት ጊዜ አንስቶ የቀጠለው ግልጽ ጥላቻ የሰፈነበት ዘመን ናቸው።

እ.ኤ.አ. በ1947 እስራኤላውያን ከተበታተኑበት የዓለም ክፍል ተሰባስበው መንግሥት ለመመሥረት ሲጠይቁ በአንግሊዝ እጅ የነበረችው ፍልስጤም ለሁለት ትከፈል ወይስ አትከፈል የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ከተቃወሙት 13 ሀገራት መካከል ኢራን አንዷ ነበረች።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት ያባባሰው ምንድን ነው?

በአያቶላ ኮሜኒ የተመራው የ1979 የኢራን እስላማዊ አብዮት የፓህላቪ ሥርወ መንግሥትን በማስወገድ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ዓለማ ያደረገው የእስልምናውን ዓለም ለማነቃቃት እና የእስልምና እሴቶችን ከፍ ለማድረግ ነበር።

አብዮቱ እስራኤል እና ቴህራን የነበራቸውን ግንኙነት በአስገራሚ ሁኔታ ቀይሮ የፍልስጤማውያን ደጋፊ ሆነ። ይህ ጉዳይ ደግሞ ኢራን ከእስራኤል በተጨማሪ የመካከለኛውን ምሥራቅ አንኳር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አካል አድርጋ ለምትከታተለው እና የእስራኤል ወዳጅ ለሆነችው አሜሪካ ያልተዋጠ ጉዳይ ነበር፡፡

የኢራን ኢስላማዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት እና ከ1979 እስከ አሁን ድረስ ሥልጣን የያዙት ሰባቱም የሀገሪቱ መሪዎች ንግግሮች እና የሥልጣን ቆይታዎች የሚያረጋግጠው የኢራን አብዮታዊ መንግሥት የሺዓ እስልምና አስተሳሰብን ማስፋፋት ነው።

በዚህ ምክንያትም ይህን እንቅስቃሴ በመካከለኛው ምሥራቅ እንደተፈጠረ እንቅፋት የተመለከተችው አሜሪካ እና በእስልምናው ዓለም እኛ ወሳኞች መሆን አለብን የሚሉት እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ሀገራት ኢራን ላይ ጥርሳቸውን ነከሱ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለረጅም ጊዜ አቋርጣ የቆየችውም በዚሁ መነሻ ሲሆን፣ በቅርቡ በቻይና አቀራራቢነት ግንኙነታቸውን ማደስ ቢጀምሩም በእስልምናው ሴክት ልዩነት እና በቀጠናው የበላይነትን ለመያዝ ያለው ፉክክራቸው ግን አሁንም በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓቸው እንደቀጠለ ነው፡፡

ሁለቱም ሀገራት አንዱ የአንዱን መኖር አለመፈለጋቸው ጠላትነታቸው ያመረረ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ምክንያትም እስራኤል ኒኩልየር ስትታጠቅ ኢራን በተለያዩ ጊዜያት ያደረገቻቸው ሙከራዎች በእስራኤል ቀጥተኛ ተፅዕኖ (ማለትም የኢራንን የኒኩሊየር ሳይንቲስቶች በመግደል እንዲሁም የተቀናጀ የሳይበር ጥቃት በመፈጸም) እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጫና ኢራን ኒኩልየር መታጠቋን ባታውጅም የጦር መሣሪያ እና የሠራዊት ዝግጅቷ ግን ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

አሜሪካ እና አጋሮቿ ኢራን እንደልብ እንዳትንቀሳቀስ በማዕቀብ እያደቀቋት ሲሆን፣ ኢራን በበኩሏ የነሱ ተቃራኒ የሆኑ የታጠቁ ቡድኖችን ሁሉ ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ ለዚህም የየመኑ ሁቲ እንዲሁም በሊባኖስ እና ሶሪያ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ይህ የአሜሪካ መሩ ምዕራባውያን ጫና ደግሞ ኢራንን አዳክሞ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ከማምጣት ይልቅ የበለጠ እንዲጠናከሩ እና ለጽዮናዊነት እና ምዕራባውያን ያላቸው ጥላቻ እንዲባባስ ያደረገ ነው፡፡ "TONY BLAIR INSTITUTE FOR GLOBAL CHANGE" ላይ የታተመው ጥናት እንደሚያመለክተው በምዕራባውያን በሺዓ እስልምና መሩ የኢራን መንግሥት ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ኢራንን እንደፈለጉት ከማዳከም ይልቅ፡- ርዕዮተ ዓለሙ እንዲሰርጽ እና የኢራን ሕዝብ አንድነት ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል፤ የእስልምና አብዮቱ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ ሀገሪቱ ጠንካራ አቋም እንዲኖራት ገፊ ምክንያት ሆኗል፤ የ2015 ዓለም አቀፍ የኒኩልየር ስምምነት የኢራንን ፀረ-አሜሪካ አቋም አልለወጠም፤ እስራኤልን ለማጥፋት ያለመው ቁርጥ ውሳኔ በኢራን ተቋማት ውስጥ ሥር ሰዷል፡፡

ከሁሉ ይበልጥ በ2020 ታዋቂው የኑክሌር ሳይንቲስት ሞሰን ፋክሪዛዴ በሳተላይት የታገዘ የርቀት መቆጣጠሪያ ያለው መሣሪያ በመኪናው ጀርባ ላይ ተገጥሞ ተገድሎ መረጃውም ደብዛው እንዲጠፋ ከተደረገ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ባላንጣነት እና በየጥቅሞቻቸው ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተባባሰ መጥቷል። እናም ቀድሞውንም በቋፍ የነበረው የሁለቱ ተቀናቃኞች ጠላትነት ወደማይታረቅበት ደረጃ አድጓል፡፡

የኢራን መጠነ ሰፊ ጥቃት አንድምታ

የፍልስጤም ጉዳይ ለበርካታ አስርት ዓመታት ለዘለቀው የእስራኤል እና ኢራን ሥር የሰደደ ጥላቻ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። እስራኤል ከጋዛ ባሻገር ጥቃቶችን እያሰፋች በመምጣቷ ኢራን በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ጣልቃ እንደምትገባ ስትዝትም ቆይታለች። እስራኤል ደግሞ ጥቃቷን አስፍታ የቴህራን ከፍተኛ ተጽዕኖ ባለባቸው በሊባኖስ እና በሶርያ የቦምብ ጥቃቶችን ሰንዝራለች፡፡

ኢራን ከሁለት ሳምንታት በፊት በሶሪያ በሚገኘው ቆንሲላዋ ላይ በእስራኤል ለተሰነዘረ ጥቃት አጸፋ ነው ያለችውን በመቶዎች በሚቆጠሩ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች የታገዘ ጥቃት እስራኤል ላይ ፈጽማለች። በተጨማሪም የእስራኤል ንብረት ነው ያለችውን መርከብም አግታለች፡፡

ከኢራን ጥቃት በፊት በአካባቢው ሊከሰት የሚችለው ቀውስ ያሳሰባቸው ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ የአየር ክልላቸውን ለጊዜው ዘግተው የነበረ ሲሆን፣ ሶርያ ደግሞ በደማስቆ እና በዋና ዋና ወደቦቿ ዙሪያ ፓንትዚር የተባለውን ሩሲያ ሠራሽ የአየር መከላከያ መሣሪያዎቿን አንቅታ ነበር።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ጥቃቱ ጽዮናዊቷ እስራኤል በሶርያ ውስጥ በሚገኘው የኢራን ቆንጽላ ላይ ለፈጸመችው ወንጀል ቅጣት መሆኑን አረጋግጧል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ተወካይ እንዳሉት እስራኤል ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ስህተት ከሠራቸ አጸፋው የከፋ ይሆናል፡፡

በሶሪያ በሚገኘው የኢራን ቆንጽላ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነት ያልወሰደችው እስራኤል በበኩሏ ከፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ኃላይሎች ጋር በመሆን በኢራን የተሞከሩባትን ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃቶችን 99 በመቶ አክሽፌያለሁ ብላለች።

አሜሪካ ኢራን ለድርጊቱ ዋጋ ትከፍላለች ያለች ሲሆን፣ በአካባቢው ላይ ያለው ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲቆም አድርጋለች፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በለፈው ቅዳሜ ከብሔራዊ የደህንነት ቡድናቸው ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተዋል። ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒሰትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ዋሽንግተን ለአጋሯ እስራኤል ደህንነት ያላትን ጠንካራ ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የኢራን ጥቃት በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ቀጣይ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል ተብሎ በተፈራበት በአሁኑ ሰዓት ግብፅ እና ሳዑዲ ዓረቢያ ሁለቱም ሀገራት እርስ በርስ ከመጠቃቀት እንዲታቀቡ ጠይቀዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ደግሞ በእስራኤል ጥያቄ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም የኢራንን ጥቃት አውግዘው፣ "ጥቃቱ በአካባቢው ላይ የማያባራ አውዳሚ አደጋ ሊጋብዝ ይችላል" ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያ ምክትል አምባሳደር ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ የኢራን ጥቃት ራስን የመከላከል መብትን የሚያጎናጽፈው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አካል እንደሆነ በመግለጸ አሰላልፉን ተጠባቂ አድርገውታል። "እስራኤል ለዚህ ጥቃት ምላሽ ከሰጠች ኢራን ከአሁኑ የላቀ እና አውዳሚ የሆነ ምላሽ እንደምትሰጥ እርግጠና ነኝ" ሲሉም አክለዋል።

ሁልጊዜም ግልጽ በሆነ የሁለትዮሽ ውዝግብ ውስጥ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ የምትታወቀው ቻይና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንደተለመደው ሁሉም ወገኖች ውጥረትን ከሚያባብስ ድርጊት እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርባለች። ሁኔታው የጋዛ ቀውስ ውጤት መሆኑን የጠቀሰችው ቻይና፣ ከዚህ የከፋ ቀውስ በቀጠናው ላይ ከመከሰቱ በፊት እስራል በጋዛ ላይ የጀመረችውን ዘመቻ ማቆም አለባት ብለዋል።

የፖለቲካ ተንታኞች ግን ኢራን በእስራኤል ላይ የፈፀመችው ጥቃት ተጨማሪ ቀውስን በአካባቢው ላይ እንደይፈጥር በጥንቃቄ የተከናወነ ነው ይላሉ። የኳታር ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ሀሰን ባራሪ "ኢራን የፈጸመችው ጥቃት ደካማ እንዳልሆነች ለማሳየት እና ራሷን መከላከል እንደምትችል ለማረጋገጥ በጥንቃቄ የተፈጸመ ብለውታል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በጋዛ ያለውን ሁኔታ የበለጠ ሊያወሳስበው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የካርኔጊ የመካከለኛው ምሥራቅ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ማሃ ያህያ በበኩላቸው አሁን ቴህራን በውክልና ሳይሆን ወደ ቀጥተኛ ጦርነት ለመግባት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች ብለዋል፡፡ አክለውም "ይህ እየመጣ መሆኑን በቂ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፤ ድሮኖቹ እና ሚሳኤሎቹ የእስራኤል ግዛት ከመድረሳቸው በፊት ተመትተው እንደሚወድቁ ቢያወቁም ዓለማቸውን አሳክተዋል" ይላሉ፡፡ አሜሪካ ጉዳዩን ለማብረድም ሆነ ለማባባስ ዕድሉ በእጇ እንደሆነም ያህያ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አሜሪካ በቀጥታ ኢራንን ለመውጋት ምክንያት ስታጣ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ በማስገባት በዚህ ሰበብ ልታጠቃት እንደምትፈልግም የፖለቲካ ተንታኞች ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top