ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

16 Days Ago
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እያጋጠመ ያለውን አደጋ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በናይሮቢ፣ ኬንያ በተካሄደው የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (አይ ዲ ኤ) ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፥ የአፍሪካ ቀንድ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰቱ የተለያዩ አደጋዎች ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ እነዚህን ስጋቶች ለመቀነስ ለአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በመርሃ ግብሩ ደንን መልሶ ማልማት፣ አረንጓዴ ልማትን ማጠናከር እንዲሁም የአካባቢ ልማት ጥበቃን ማጎልበት ላይ አተኩራ እየሰራች ነው ብለዋል። 

ለኑሮ የሚመች አካባቢን መፍጠር የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን በመጠቆም፥ ምቹ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል። 

መንግሥት ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን እንደምሳሌ አንስተዋል። 

በዚህም በሀገሪቱ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታት እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እውን ለማድረግ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝምና በሌሎች የልማት ዘርፎች የ10 ዓመት የልማት እቅዶች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል። 

በትምህርት፣ በዲጂታላይዜሽን እና በኃይል አቅርቦት ዘርፎች እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ስራዎችን እና ውጤቶችንም ለአብነት አንስተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናው ለእርቅ እና ለምክክር ቅድሚያ በመስጠት መሰራት እንዳለበት አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ እርቅ እና ምክክር እውን እንዲሆን ያከናወናቸውን ተግባራትም ጠቅሰዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top