የውጭ ባለሐብቶች ክልከላ ተደርጎባቸው በነበሩ የሀገር ውስጥ ገበያ ለመሳተፍ ከመግባታቸው በፊት ሳቢ የፋይናንስ ፖሊሲ ለውጦች ሊደረጉ ይገባል፡- የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች

10 Days Ago 260
የውጭ ባለሐብቶች ክልከላ ተደርጎባቸው በነበሩ የሀገር ውስጥ ገበያ ለመሳተፍ ከመግባታቸው በፊት ሳቢ የፋይናንስ ፖሊሲ ለውጦች ሊደረጉ ይገባል፡- የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች

የውጭ ባለሐብቶች ክልከላ ተደርጎባቸው በነበሩ የሀገር ውስጥ ገበያ ለመሳተፍ ከመግባታቸው በፊት ሳቢ የፋይናንስ ፖሊሲ ለውጦች እና ምቹ የስራ ከባቢ ሊፈጠር እንደሚገባ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለውጭ ባለሐብቶች ክልከላ ተደርጎባቸው የነበሩ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሁም የገቢና ወጪ ንግድ ላይ ባለሐብቶቹ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል:: በአጭር ጊዜ ውስጥም ይህንኑ የሚፈቅድ መመሪያ ወጥቷል፡፡

ሕጉ ለውጭ ባለሐብቶች ንብረት ማፍራትና ተያያዥ መብቶችን የሚሰጣቸው መሆኑም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ይሄንንም ተከትሎ ኢቢሲ ሳይበር ያነጋገራቸው የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) እና  ብርሀኑ ደኑ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ ገበያ መሳተፋቸው ለኢኮኖሚው በርካታ ጥቅም እንዳለው ገልጸው፤ ባለሐብቶቹ ወደ ሀገር ከመግባታቸው በፊት ሳቢ የፋይናንስ ፖሊሲ ለውጦች እና ምቹ የስራ ከባቢ ሊፈጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተደርጎ የነበረው ክልከላ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያደርስ መቆየቱን የሚገልጹት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ፤ ባለፉት ጊዜያት ሲከሰት የነበረው ከፍተኛ የዋጋ ንረት የዚሁ ውጤት ስለመሆኑም ያነሳሉ።

የውጭ ኩባንያዎች በችርቻሮ ንግድ ላይ እንዳይሰማሩ መከልከሉ ተገቢ እንዳልነበር የሚያወሱት ባለሙያው፤ ባለሐብቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው መስራታቸው ለሸማቹ የዋጋ ንረትን ከማረጋጋት ባሻገር የሀገሪቷን የግብይት ሁኔታ በሕግ እና በስርዓት እንዲመራ ያስችለዋል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የውጭ ባለሐብቶቹ ወደ ገበያው ሲቀላቀሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ይዘው ስለሚመጡ የሀገር ውስጥ አርሶ አደሮች በበቂ ሁኔታ እንዲያመርቱ በማድረግ እና ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ይገልጸሉ፡፡

የውጭ ልምድ ያላቸው ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ የምርቱን ጥራት እና እሴት መጨመር ያስችላል ብለዋል፡፡

አክለውም፤ ኩባንያዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው በሀገሪቷ ያሉ የገበያ መዋዠቆችን የሚያስቀሩ እና በማምረት ስራ የተሰማሩ አካላትንም የሚያበረታታ ከመሆኑም ባሻገር የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሊያድጉበት የሚችሉበት መንገድ  ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡

ባለሐብቶቹ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይዘው እንደሚመጡ የሚገልጹት ባለሙያው፤  ኢንቨስትመንታቸውን ሊመልሱ የሚችሉበት የገበያ ስርዓት ሊፈጠር እንደሚገባ ነው የሚያነሱት፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ብርሀኑ ደኑ (ዶ/ር ) ይሄንኑ ሀሳብ ይጋሩታል፤ የውጭ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ ገበያ ከመሳተፋቸው በፊት ሳቢ የሆኑ የፋይናንስ ፓሊሲዎችን ማውጣት እና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

የውጭ ባለሐብቶቹ በሀገር ውስጥ ገበያ መሳተፋቸው ለኢኮኖሚው በርካታ ጥቅም አለው የሚሉት ባለሙያው፤  ለወጣቱ ከፍተኛ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የሀገር ውስጥ አምራቾች ምርታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ እና ተፎካካሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ፡፡

አክለውም እስካሁን ድረስ ተዘግቶ የነበረው ዘርፉ ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ክፍት መሆኑ በችርቻሮ እና በጅምላ ንግድ ዙሪያ የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ እጥረቶችን ይቀርፋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቷ ያለው የግብይት ስርዓት አስቸጋሪ እና ኋላ ቀር ነው ያሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ብርሀኑ፤ የውጭ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረጋቸው ከመንግስት ብቻ ይጠበቅ የነበረውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ወደ ግል ባለሀብቱ በማስተላለፍ ለኢኮኖሚው ጥሩ ግብዓት እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

በተስሊም ሙሀመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top