ያልተዘመረላቸው ጀግና - ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ

14 ቀን በፊት
ያልተዘመረላቸው ጀግና - ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ

ከራሳቸው ጥቅም በላይ የሀገር ፍቅር የነበራቸው፤ በጀግንነት ለሀገራቸው ሉዓላዊነት የታገሉ የሀገርን የነፃነት ጠብቀው ያቆዩ ባለገድል እና ባለታሪክ ከሆኑ ጀግኖች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ደቡሳ፡፡

ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ደቡሳ ከአዲስ አበባ 104 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወሊሶ ማሩ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በ1897 ዓ.ም ተወለዱ ፡፡

ከልጅነታቸው ጀምሮ ጥልቅ የሀገር ፍቅር የነበራቸው ጀግና ነበሩ፡፡ በትምህርት ረገድ ፊደልን በአካባቢያቸው የቆጠሩ ሲሆን፣ የሐይማኖት ትምህርትም ተምረው በዲቁና ቤተ ክርስቲያንን እስከማገልገል ደርሰዋል፡፡

ከ1912 ዓ.ም እስከ 1918 ዓ.ም በቀድሞው የጦር ሚኒስቴር ፊታውራሪ ሀብተዮርጊስ አስተዳደር ውስጥ ወታደራዊ ተግባራትን ተወጥተዋል፡፡

ከ1919 ዓ.ም እስከ 1924 ዓ.ም ለግርማዊ ቀዳማዊነታቸው ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት ውስጥም በጋሻ ጃግሬ ደንብ አገልግሎታቸውን አበርክተዋል፡፡

ከ1921-1928 ወደ ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን ተዛውረው በማገልገል የባላምባራስነት ማዕረግም አግኝተዋል፡፡

በ1928 ዓ.ም በነበረው የማይጨው ጦርነት ከጣሊያን ጋር ተዋግተው ተንቤን ላይ ከፍ ያላ ጀብዱ ሠርተዋል፡፡ ከ1929 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም የብዙ ሺህ አርበኞች መሪ ሆነው በየአውራጃው በመዞር ለ5 ዓመታት ከፋሺስት ጋር ተዋግተዋል፤ ለነፃነት ትርጉም ያለው እና የማይሞት ሥራ ሠርተዋል፡፡

ደጃዝማች ገረሱ ሀገራቸውን ለማገልገል ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው የአውሮፓውያን አፍሪካን ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በመቃወም ይታወቃሉ፡፡

ጣሊያን ህዝቡን በማንነቱ እና በእምነቱ በመከፋፈል እንዲጣላ አድርጎ ለመምራት የነበራትን ፍላጎት በመረዳት ይህን ክፉ ሀሳብ ታግለዋል፤ ህዝቡንም አታግለዋል ይላሉ የደጅአዝማች ገረሱ ዱኪ ልጅ ታቦር ገረሱ፡፡.

በየአወራጃው በመዞር የጣሊንን ከከፋፍለህ ግዛ የውጭ ፖሊሲ በፅኑ ተቃውመዋል፤ ሴራውን በጥበብ ገርስሰዋል፡፡ ወታደራዊ ስታራቴጂስት እና ጀግና በመሆናቸውም ከቀዳማዊ ኃይለሥለሴ እጅ ቤልጂግ ጠመንጃ ተሸልመዋል፡፡

ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርራ በነበረበት ጊዜ በህዝብ ላይ የነበረውን ያልተገባ ፍርሐት በጥበብ አፍርሰዋል፤ "ጣሊያን ቅኝ ግዛት ልትይዘን ነው፤ ባሪያ ሊያደረጉን ነው፤ ነፃነታችንን ሊገፍፉ ነው፤ ከፋፍለው ሊገዙን ነው፤ በወራሪ ፕሮፖጋንዳ መታለል የለብንም፤ አንድነታችንን መጠበቅ አለብን" በማለት ህዝቡን አረጋግተዋል፡፡

በእምነት እና በሌሎች ተፈጥሯዊ ልዩነቶች መካፋፈል የለብንም ይልቁንስ ተባብረን አንድነታችንን ማጠናከር አለብን በማለት ስለ አንድነት ቀስቅሰዋል፡፡

ጣሊያን ለሴራው ይጠቀምበት የነበረውን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የተረዱ እና በህዝብ መካካል ልዩነት ቢኖር አንኳን እኛ ራሳችን መፍታት አለብን የሚል እምነት እንደ ነበራቸው ልጃቸው ይናገራሉ፡፡ "ጠላት እኛን በራሳችን ጉዳይ ሊዳኘን አይገባም የሚል ስሜት እና አቋም ነበረው" ይላሉ ልጃቸው አቶ ታቦር፡፡

በ1958 ዓ.ም በ61 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አርበኛ እና ጀግና ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፤ ትውልድ ከጀግንነታቸው አንዲማር በተወለዱበት አካባቢ በስማቸው ትምህርት ቤት ተሰይሟል፤ መኖሪያ ቤታቸውንም ወደ ሙዚየምነት ተቀይሮ ታሪክን ለትውልድ እያስተላለፈ ይገኛል፡፡

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top