"አባቶቻችን በአርበኝነት ተጋድሎ ነፃነቷን አስከብረው ያቆዩልንን ሃገር አፅንተን ማቆየት የሁላችንም ኃላፊነት ነው" - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

13 Days Ago
"አባቶቻችን በአርበኝነት ተጋድሎ ነፃነቷን አስከብረው ያቆዩልንን ሃገር አፅንተን ማቆየት የሁላችንም ኃላፊነት ነው" - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

83ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የአርበኞች መታሰቢያ ሐውልት በሚገኝበት ስፍራ ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ የአርበኞች ማህበር የበላይ ጠባቂ ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ የጥንት አባቶቻችን በአርበኝነት ተጋድሎ ነፃነቷን አስከብረው ያቆዩልንን ሃገር እና ነፃነት አፅንተን ማቆየት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ትላንት አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ነፃነት ህይወታቸውን መስዋዕት ከፍለውልናል ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ አሁን ያለነው ትውልድ ደግሞ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን በተባበረ ክንዳችን ድል ነስተን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ በትጋት መስራት አለብን ሲሉ ገልፀዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የኢፌድሪ መከላከያ ሰራዊትን በመወከል የተገኙት የመከላከያ የሰው ሀብት አመራር ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ሀጫሉ ሸለመ፤ አርበኝነት በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥል የኢትዮጵያዊያን መገለጫ እሴት ነው ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊትም ይህንኑ የጀግኖች አርበኞች እሴትን ተላብሶ ለሃገሩ አንድነትና ሉአላዊነት አኩሪ መስዋእትነት እየከፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ የአርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው፤ ዛሬ ላይ እያከበርን ያለው የድል በዓል ትላንት ኢትዮጵያዊያን ለባእዳን ሃገር ላለመገዛት እና የኢትዮጵያን የቀደመ የጀግንነት ታሪክ ጥላሸት ላለማስቀባት የከፈሉት መስዋእትነት በመሆኑ ትውልዱ ይህን ታሪክ አስቀጥሎ ማለፍ እንዳለበት አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የመከላከያ የሰው ሃብት መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ሀጫሉ ሸለመ እንዲሁም የጥንታዊት ኢትዮጵያ የአርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ የጀግኖች መታሰቢያ ሃውልቱ ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top