የበጋ መስኖ ልማት የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት ነው - አቶ አወል አርባ

12 ቀን በፊት
የበጋ መስኖ ልማት የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት ነው - አቶ አወል አርባ

የበጋ መስኖ ልማት ከምርታማነት ባለፈ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት የልማት ስኬት መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚገነቡ አነስተኛና መካከለኛ ግድቦችም ለመስኖ ልማት ሥራዎች እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በግብርና እና አርብቶ አደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም በክልሉ ከአርብቶ አደርነት፣ ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በመሸጋገር ሂደት በግብርና ልማት ስኬት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በርካቶች በተለይም የበቆሎ፣ የጥጥ፣ የማሽላና የስንዴ ሰብል ልማት ላይ እየተሰማሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በአፋር ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዲስ የግብርና ተሞክሮ መሆኑን ተናግረው፤ ከምርታማነት ባለፈ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት የልማት ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

የዘርፉ ልማት የክልሉን እምቅ የውሃ እና የመሬት አቅም በመጠቀም ምርታማ እያደረገና ከአርብቶ አደርነት፣ ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በማሸጋገር ሂደት የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ሙዝ፣ ማንጎና የሽንኩርት ምርት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ የግብርና ልማት የአርብቶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የተሻለ ህይወት እንዲመራ እያስቻለው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በክልሉ የጎርፍ አደጋን ለመከላከልና ለመስኖ ልማት የተገነቡት የከሰምና ተንዳሆ ግድቦች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

ግድቦቹ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባለፈ አርብቶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ውሃ በቅርበት እንዲያገኝ እያስቻሉ መሆኑን አንስተዋል። 

በክልሉ የአነስተኛና የመካከለኛ ግድብ ግንባታ በማከናወን በጊዜያዊነት የጎርፍ አደጋን የመከላከል በቋሚነት ደግሞ ግድቦችን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top