የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ እና የ2063 አጀንዳን ለማሳካት ከውጭ ተፅዕኖ መላቀቅና በትብብር መስራት ወሳኝ ነው ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር አየለ በከሬ የአፍሪካ ተስፋ እና ፈተናዎች ምንድናቸው በሚል በተዘጋጀው የኢቲቪ 'ዳጉ' ፕሮግራም ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተጠዋል፡፡
አፍሪካ እምቅ ሐብቷን በመጠቀም ማደግ ያልቻለችው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በመቀጠሉ መሆኑን ነው የታሪክ ተመራማሪው የሚገልጹት፡፡
አህጉሪቱ ያላትን ሐብት ተጠቅማ ለማደግ የነበራትን እድል ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዓለም ሥርዓት በመቀየሩ በውጭ ኃይሎች ስግብግብ ፍላጎት መጨናገፉን ጠቅሰዋል፡፡
አፍሪካን ማሳደግ የሚችሉ እድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች በባርነት ወደ አውሮፓ መወሰዳቸውንም አንስተዋል፡፡
አፍሪካውያን በተባበረ ክንድ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ማስወገድ ቢችሉም፤ የውጭ ኃይሎች ሐብቷን ለመዝረፍ የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በመዘርጋታቸው የቀድሞ አፍሪካውያን መሪዎች ህልም በሚፈለገው መጠን አለመሳካቱን ነው የሚናገሩት፡፡
አሁንም ድረስ በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት የውጭ ሀገራት ድጋፍና ጣልቃ ገብነት ያረፈበት ስለመሆኑ ነው የሚገልጹት፡፡
እነዚህ ሃገራት ከአህጉሪቱ በሚወሰዱ ጥሬ እቃዎች እሴትን በመጨመር ራሳቸውን ማበልጸግ መቻላቸውን ገልጸው፤ አፍሪካ ግን አሁንም በግጭት አዙሪቱ ውስጥ ትገኛለች ብለዋል፡፡
በአፍሪካ የህዝብ ድምፅ የሚሰማበት እና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት ሥርዓት ካልተዘረጋ፣ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መረዳት ይገባል ይላሉ ፕሮፌሰር አየለ፡፡
የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063ትን ለማሳካት ከ60 እስከ 70 በመቶ ከአውሮፓ ህብረት የሚያገኘውን በጀት በራሱ መሸፈን መቻልና ሀገራቱ አንድነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ነው ተመራማሪው የሚያስገነዝቡት፡፡
አውሮፓውያን በአፍሪካ ለፈጸሙት ግፍ በይፋ ካሳ እንዲሰጡ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 38ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳ እንዲሆን መጀመሩ ተገቢ ስለመሆኑ ነው የገለጹት፡፡