ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በበርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጫና ውስጥ ሆኖም በሕዝብ ላብ የተገነባ ነው ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ ዓለም አቀፋ ማኅበረሰብ የነበረውን እሳቤ እንዲያሻሽል የመሰረተ ልማቱ እና የገፅታ ግንባታው እኩል ሲከናወን ቆይቷል።
በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋ ግድቡን አጠናቅቃ ለመመረቅ ዋዜማው ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ "እንኳን ደስ አለሽ!” ከሚሏት በተቃራኒ የቅኝ ገዥ አስተሳሰባቸውን ይዘው ብቅ የሚሉ የሩቅም የቅርብም አገራት እንደሚኖሩ ተገማች ነው፡፡
ለዚህም ማሳያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብፆች በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ለሕዝብ እንደራሴ ከገለፁ በኋላ የተሰሙ ማጉረምገሞች ማሳያ መሆናቸውን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ሚፍታህ መሀመድ ገልፀዋል፡፡
የዓረብ ሀገራትን በሚወክሉ ጉዳዮች ላይ ቀዳሚ ሆና የምትንቀሳቀሰው ግብፅ ይህ እንቅስቃሴዋ ከተለያዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት መሪዎች ጋር ያዋላት እና ከቢሯቸው እንድትቆይ እድል የፈጠረላት መሆኑን አቶ ሚፍታህ ለኢቢሲ ዶትስተሪም ተናግረዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብንም በተመለከተ የሚሰራጨውን የተዛባ መረጃን በማሰራጨትና እና ነገሮችን መልክ ቀይሮ በማሳየት በእጅ አዙር ጫና ለመፍጠር ያደረገቸው ሙከራ የቅርብ ዓመታት ትውስታ ናቸው ይላሉ ተመራማሪው፡፡
በውሃ ግድብ ግንባታዎች ጉዳይ ላይ ተሰብስቦ የማያውቀው የፀጥታው ምክር ቤትም ጉዳዩን በተደጋጋሚ እንዲያየው ማድረጓን የግብጽ ጫና ለማሳደር ከምታደርጋቸው ሙከራዎች አንዱ ማሳያ መሆኑን በዋቢነት አንስተዋል።
በመጪዎቹ ጊዜያት ግብፅ እነዚህን ጫናዎች እንዲቀጥሉ የአውሮፓ ሕብረት ብሎም የአፍሪካ ሕብረትም ጫና በመፍጠሩ እንዲሳተፉ ለማድረግ እንደምትጥር ይገመታል ሲሉ ምሑሩ ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያም በበኩሏ እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ትክክለኛ ግንዛቤ ለመፍጠር መስራት እንዳላለባት አመላክተው፤ አዲስ የዲፕሎማሲ መንገድ መጀመር ቀዳሚው የመፍትሄ ሃሳብ መሆኑን ተመራማሪው ሚፍታህ ይናገራሉ፡፡
ሀገራቱ ቀድሞም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን የአብረን እንልማ ግብዣ በአግባቡ የሚረዱበትን ትክክለኛ ዐውድ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ፡፡
በናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ስር የተደረገውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ያልፈረሙ ሀገራት እንዲፈርሙ ማድረግ ሌላው በሳል የዲፕሎማሲ እርምጃ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የሚነሱ ጉዳዮችን የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን በሚለው የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ በኩል እንዲታዩ ማስቻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በመግለፅ፤ በግድቡ ጉዳይ የሚነሱ አደራዳሪ ሀገራት ከተደራዳሪ ሀገራት ጋር ያላቸውን መስተጋብር ማጤን ብሎም መመርመር ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በገፅታ ግንባታ ረገድ መረጃ መለዋወጥ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግ የራሱ በጎ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የጠቀሱት፡፡
በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለተፋሰሱ ሀገራት ያለው ጠቀሜታ ማስረዳት፤ እንዲሁም ከረጅም ጊዜ ዕቅዶች ጋር በማጣቀስ በዓባይ ወንዝና በግድቡ ላይ አስረጂ እና ገላጭ የዶክመንተሪ መረጃዎችን በስፋት ማዘጋጀትና ማሰራጨት መሥራት ወሳኝ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡
ሃሳባቸውን ሲጠቀልሉም የሚመጣውን ጫና ብሎም የእጅ አዙር እርምጃዎችን በጥንቃቄ በማጤን በተሻለ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ አፅንኖት ሰጥተዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBC #ebcdotstream #GERD #ItIsMyDam #SelfReliance