42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ነገ ይጀመራል

1 Yr Ago
42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ነገ ይጀመራል

42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ነገ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይጀመራል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የሕብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች ይሳተፋሉ።

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው።

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮሞሮስ፣ ታንዛንያ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሴራሊዮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዚምባቡዌ እና ማሊ ይገኙበታል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በጥር ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው 45ኛ መደበኛ ስብሰባ የተወያየባቸው አጀንዳዎች እንደሚቀርቡበት ሕብረቱ አስታውቋል።

ኮሚቴው በስብሰባው እ.አ.አ በ2022 የሕብረቱ መሪ-ቃል ትኩረት በነበረው የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎች አፈጻጸም መገምገሙ የሚታወስ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት በሚያደርገው ስብሰባ በኮሚቴው የቀረቡለትን የተለያዩ አጀንዳዎች ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

ምክር ቤቱ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ የ2023 መሪ ሃሳብ ሆኖ እንዲሰየም በቀረበው የመነሻ ሃሳብ ላይ እንደሚወያይ የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በውይይቱ ያጸደቃቸውን አጀንዳዎች ለ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ያቀርባል።

የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top