በ14 ዓመቷ 3 መፅሐፍትን በማሳተም በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን ያሰፈረችው ታዳጊ

1 Mon Ago
በ14 ዓመቷ 3 መፅሐፍትን በማሳተም በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟን ያሰፈረችው ታዳጊ

በልጅነት ዕድሜ የ3 መፅሐፍት ደራሲ መሆን አይደለም፤ መፅሐፍትን አንብቦ ለመረዳት በአብዛኛው የወላጆች ድጋፍ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ለ14 ዓመቷ ደራሲ ሪታ ሁሴን አልሃዚ ግን ይህ ከባድ አልነበረም።

ታዳጊዋ ደራሲ ሪታ ሁሴን አልሃዚ የተወለደችው በምስራቃዊ ሳኡዲ ዓረቢያ ዳኅራን ግዛት ውስጥ ነው።

ዓረብኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፋ መናገር እና መፃፍ የምትችለው ሪታ፤ አሁን ላይ ጃፓንኛ ቋንቋ እየተማረች ነው። 

ሪታ የ6 ዓመት ሕፃን እያለች ነበር ወላጆቿ ለትምህርት ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሌላ ሀገር ሲሄዱ የስኬት መንገዷን አንድ ብላ የጀመረችው።

የተለያዩ አስተማሪ ታሪኮችን የማጥናት፣ የማወቅ እና የማንበብ ልምድ የነበራት ሪታ፤ በ7 ዓመቷ ወደ ቤተ-መፅሐፍት በመሄድ አጫጭር ታሪኮችን ማንበብ እና መፃፍ ጀመረች።

ሪታ በ11 ዓመቷ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2019 "ትሬዠር ኦፍ ዘ ሎስት ሲ" በሚል ርዕስ የመጀመሪያዋ የሆነውን ልብ-ወለድ መፅሐፍ አሳተመች።

በቀጣዩ ዓመት በ12 ዓመት ከ295 ቀናት ዕድሜዋ ደግሞ "ፖርታል ኦፍ ዘ ሂድን ዎርልድ" በሚል ርዕስ ሁለተኛ መፅሐፏን ማሳተም ችላለች።

በልጅነት ዕድሜዋ ቤተ-መፅሐፍት በመሄድ የንባብ ልምድ ያዳበረቸው ታዳጊ፤ ሦስተኛውን መፅሐፏን "ቢዮንድ ዘ ፊውቸር ዎርልድ" በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅታለች።

በዚህም ሦስት መፅሐፍትን በማሳተም ታዳጊ ሴት ደራሲ በመባል ስሟን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ማስፈር ችላለች።

ዕምቅ የሥነ-ፅሁፍ ጥበብ እንዳላት የሚነገርላት ታዳጊዋ፤ አሁን ላይ አራተኛ መፅሐፏን "ዘ ፓሴጅ ቱ ዘ አንኖውን" በሚል ርዕስ እየፃፈች እንደሆነም ነው የተገለጸው። 

ለአዋቂዎች የሚከብደውን መፅሐፍ የማሳተም ስራ በታዳጊ ዕድሜዋ ማሳካት በመቻሏም አድናቆት እየተቸራት ትገኛለች።

ጥሩ ታሪክ ያለው መፅሐፍ ለመፃፍ ጥሩ የመፅሐፍ አደረጃጀት ወሳኝ መሆኑን የምትናገረው ሪታ፤ የራሷን መፅሐፍት በመከለስ ጥንካሬዎቿን ለማስቀጠል እና ድክምቶቿን ለማረም እንደምትጠቀምበት ትገልጻለች። 

ህፃናት የታሪክ ፀሐፊ፣ አንባቢ፣ ተራኪ እና ተናገሪ  እንዲሆኑ ጉትት እና ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል ባይ ናት።

ጥሩ ደራሲ ለመሆን ልምድ እና ትምህርት ያስፈልጋል የምትለው ታዳጊዋ፤ የመፃፍ ልምዷን ያዳበረችው የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ጭምር ስለመሆኑም ትናገራለች።

ሪታ በዚህ ለጋ ዕድሜዋ ለዓለም ያበረከተቻቸው መፅሐፍት እና አሁንም እየሰራች ያለችው ስራ በርካታ ታዳጊዎችን የሚያነቃቃ እንደሆነ ታምናለች።

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top