የከተሞች ወግ- መካ

1 Mon Ago
የከተሞች ወግ- መካ

የምድራችን ትልቁ መስጅድ መገኛ፣ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ያላት፣ በየዓመቱ ከ2 እስከ 4 ሚሊዮን የሀጅ እና የኡምራ ተጓዦችን ተቀብላ የምታስተናግድ፣ እንዲሁም በእስልምና እምነት ቅዱስ ስፍራነት የምትታወቀው መካ ከተማ በሳዑዲ ዓረቢያ ሄጃዛ ግዛት ውስጥ ትገኛለች።

ስፋቷ 1 ሺህ 200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይኖርባታል። ከቀይ ባሕር 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

በሀገሪቱ ከሪያድ እና ከጂዳ ከተሞች ቀጥሎ 3ኛዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚኖርባት ከተማ ናት። በሳዑዲ ዓረቢያ መካህ አልሙከረማህ በሚል ትጠራለች።

መካ የሚለው ቃል በርካታ ትርጉሞች ቢኖሩትም በአብዛኛው ካአባን ጨምሮ ቅዱስ ስፍራ የሚለው መጠሪያ ይገልጸዋል።

ለሃይማኖታዊ ዓላማ የሀጅ እና የኡምራ ተጓዦች መዳረሻ በመሆን በእስልምና እምነት ውስጥ ትልቅ ቦታ አላት።

በከተማዋ ከሚኖረው ህዝብ መካከል 45 በመቶ የሚሆኑት የሀገሪቱ ዜጎች ሲሆኑ፣ 55 በመቶ የሚሆኑት የሌሎች ሀገራት ዜጎች ናቸው።

9 ሚናራዎች ያሉት የዓለማችን ግዙፉ መስጂድ ማስጂደል ሀራም በአንድ ጊዜ 2 ሚሊዮን ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል።

ከተማዋ ከ318 ስፍራዎች ደረቅ ቆሻሻን በማሰባሰብ ከመሬት በታች በተዘረጋ 30 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ቦይ የቆሻሻ የማስወገጃ ሥርዓት ዘርግታለች። ይህም በዓለም ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ያላት ከተማ ያደርጋታል።

የዓለም ሙሊሞችም ሰላት በሚሰግዱበት ወቅት ፊታቸውን(ቂብላ) የሚያደርጉት ወደ ካአባ ሲሆን፣ ይህ ስፍራ በመካ ከተማ ውስጥ ይገኛል።

በረመዷን ወር ወደ መካ የሚደረግ ጉዞ ለሐጅ የሚሄዱ ተጓዦችን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል። ከተማዋ በሀጅ ወቅት በአንድ ወር ከ2 እስከ 4 ሚሊዮን የሀጅ ተጓዦችን ታስናግዳለች።

እ.ኤ.አ. በ2023 ከ10.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሃይማኖታዊ ጉዞ ወደ ከተማዋ ገብተዋል።ይህም በዓመቱ በዓለማችን በብዙ ሰዎች ከተጎበኙ አስር ከተሞች መካከል አንዷ አድርጓታል።

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ "The Fountainhead and Cradle of Islam" በሚል ትታወቃለች።

ከተማዋ ገቢ በዋናነት ለሀጅና ኡምራ ከሚጓዙ ዓለም አቀፍ የሀጅ ተጓዦች ከሚገኝ የቱሪዝም ዘርፍ ነው። ይህም ከተማዋን ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

በከተማዋ በሀጅ ወቅት ለሁጃጆች ነፃ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ 10 ሆስፒታሎች፤ በርካታ ክሊኒኮች እና ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ማዕከለት ይገኛሉ።

የእስልምና እምብርት ቅዱስ ከተማ፣ ታሪክን፣ ባህልን እና እምነትን ፍንተው አድርገው የሚያሳዩ እጅግ ዘመናዊ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች መገኛም ናት።

ክሎክ ታወር ሙዚየም፣ የአራፋት ተራራ፣ አልበርጅ አልበይት ህንፃዎች፣ የከዓባ እና የዘምዘም ውሃ ምንጮች መገኛም ናት።

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top