ለሴቶች ጥቃት መባባስ አንዱ ምክንያት የተደራጀ ህግ አለመኖሩ ነው - የህግ ባለሙያ ወ/ሮ ወይንሸት ጥበቡ

1 Mon Ago
ለሴቶች ጥቃት መባባስ አንዱ ምክንያት የተደራጀ ህግ አለመኖሩ ነው - የህግ ባለሙያ ወ/ሮ ወይንሸት ጥበቡ

ለህፃናት እና ሴቶች ጥቃት መባባስ የተደራጀ ህግ ያለመኖሩ አንዱ መንስኤ ነው ሲሉ የህግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ወይንሸት ጥበቡ ገለፁ፡፡

ህግ ህብረተሰቡን ከጥቃት ለመከላከል እና ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ ወንጀል ፈፃሚው እንዲቀጣ የሚያደርግ ነው ያሉት ባለሙያዋ፤ ወንጀል ፈፃሚው ከቅጣቱ በመማር መልካም ዜጋ እንዲሆን እና ሌላውም እርሱን ተመልክቶ እንዲማር የሚደረግበት ሂደት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በሀገሪቱ ህገ-መንግስት አንቀፅ 25 መሰረት በህግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል ስለመሆኑ የሚያመላክት መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያዋ፤ ይህም በህግ ፊት እንጂ በማህበረሰቡ ዘንድ ምን አይነት ቦታ አላቸው የሚለውን በግልፅ አያስቀምጠውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለመጀመሪያ ግዜ የወሲብ ጥቃት እና ፆታዊ ትንኮሳን ትርጉም የሰጠው የተሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 2 ንዑስ ቁጥር 11 እና 12 እንደሆነም ነው ወ/ሮ ወይንሸት የገለፁት፡፡

ጥቃትን ለማስተማርና ለመከላከል፤ ከደረሰም በኋላ ምላሽ ለመስጠት ብንፈልግ በወንጀል ህጋችን ስር የምንስተናገድ መሆኑ በተለየ መልኩ የሴቶችን ጥቃት የሚመለከት ህግ እንደሌለን የሚሳይ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም የተበታተኑ ህጎችን ማደራጀት እና በቂ ትርጉም እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

የተደራጀ ህግ የለም ከሚለው በተጨማሪ ባለው ህግ አስተማሪ ቅጣት አለመወሰዱ ተገቢ አይደለም የሚሉት ባለሙያዋ፤ ለዚህ እንደምክንያትነት ዳኞች የህግ ማቅለያ ብለው የተቀመጡ ነጥቦችን እንደሚያነሱም ተናግረዋል፡፡

የተደራጀ ህግ ካለመኖሩ ባሻገር ያለው ህግ የቅጣት መጠን አስተማሪ አለመሆኑ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ ሴቷ በተለያዩ የአካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጫና ውስጥ የምታልፍ ሲሆን ጥቃት አድራሹ ከተፈረደበት የቅጣት አመት ላይ አመክሮ ተደርጎለት መውጣቱ ለሴቷ ሌላ ቁስል መሆኑን ያነሳሉ፡፡ 

በመንግስት፣ በሲቪል ማህብረሰቡ እና በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ይህንን ለማስተካከል እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ ወይንሸት፤ እነዚህ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ግን አለመፍጠናቸውን ይተቻሉ፡፡

የሴቶች እና የወንዶች በኢኮኖሚ ያለመመጣጠን አንዱ የጥቃት መንስኤ መሆኑን የሚገልፁት ባለሙያዋ፤ ባደጉት ሀገራት የኢኮኖሚ ልዩነቱ እንብዛም ከመሆኑ የተነሳ ለፆታዊ ጥቃት የመጋለጥ እድላቸው አናሳ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ለዚህም ለአብይነት ሴቶችን ያለ ፈቃድ መከተል፣ መንካት እና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆን ይህን ያደረገ ቅጣት እንደሚወሰድበት ገልፀው፤ በሀገራችን ጥቃቅን ለሚመስሉ ትንኮሳዎች ቦታ አለመስጠታችን ጥቃቱ እንዲባባስ እንዳደረገዉ ገልፀዋል፡፡

በዚህም በቅድሚያ በማህረሰቡ ዘንድ ያለውን እሳቤ መቀየር ያስፈልጋል የሚሉት ባለሙያዋ፤ ማህበረሰቡን ማሳወቅ የአንድ ሰሞን እንቅስቃሴ ብቻ ሊሆን አይገባውም ነው ያሉት፡፡

በሴቶች ጥቃት ላይ 98 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ወንዶች እንደመያዛቸው ስልጠናው እነሱንም ያካተተ እና እንደሚመለከታቸው የሚስረዳ ሊሆን እንደሚገባውም ይጠቅሳሉ፡፡

ባለሙያዋ አክለውም ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ወንዶች የድርጊቱን አስረነዋሪነት ተረድተው እንዲያድጉ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች ማስተማር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በዘገባዎች የተፈፀመውን ወንጀል ጠቅሶ እንዲህ ተቀጣ ከማለት ባሻገር የወንጀሉን አስከፊነት እና የሚያስከትለውን ቀውስ አያይዞ ማንሳትም አንዱ አስፈላጊ ነጥብ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአፎምያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top