130 ዓመታት ከፍቅር እስከ ፖለቲካ ጉዞ

30 Days Ago
130 ዓመታት ከፍቅር እስከ ፖለቲካ ጉዞ
የብዙዎቻችን ሃሳብ ማስተላለፊያ ድልድይ ሆኖ ዓመታትን የተሻገረ፤ ትላንት ቴክኖሎጂው ባልዘመነበት ወቅት ትዝታችንን ከናፍቆት ዕውቀታችንን ከትዝብት በወረቀት አስፍረን እንድንለዋወጥ ምክንያት የሆነን የቀድሞው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖስታ።
 
ተራራ አቋርጦ ሸንተረር ሳይበግረው የሰውን ሃሳብ ፋላጎትና ምስጢር በታማኝነት በወረቀት ሰንቆ ከሚጓዝ ፖስተኛ፤ዛሬ እስካለንበት የዲጂታል ፖስታ ዘመን ለኢትዮጵያ ህዝብ የጦማር ማስተላለፊያ የሃሳብ ማንሸራሸሪያ መገናኛ ሆኖ አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል።
 
መደበኛ የፖስታ ቤት ቅርንጫፎች ከመቋቋማቸው በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖስተኛ ስራ ሙሉ በሙሉ ታማኝ ለሆኑ ግለሰቦች በአደራ ይሰጥ የነበረ ስራ መሆኑን ያውቃሉ? ተዋጊዎች ወይም የተመረጡ የተዋጊ ቤተሰብ አባላት እንደ ፖስተኛ ይሾሙም ነበር።
 
በኢትዮጵያ ፖስታ በብዕር ወዳጅነት ከፍቅር እስከ ፖለቲካ የዘለቀ ሃሳብ ተቀምሮበታል፤ ብሎም እንዲህ አይነት መረጃዎችን ለማኘት የፖስታ ሳጥን ገዝቶ ሃሳቡን ለመቀበል የፖስታ ቤቶችን ደጃፍ የጠናም ብዙ ነው።
 
ያኔ ተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲሁም መልዕክት ማድረሻ በሌለበት ዘመን የተገኘ ወዳጅ፣ የቅርብ አገልጋይ እና ዘመን ተሻጋሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ፖስታ ዛሬ ላይ የ130 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ሆኗል።
 
የተሰነዱ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ድርጅት በ1886 ዓ.ም ነበር በአዋጅ የተቋቋመው። በተቋቋመበት ዓመትም የመጀመርያዎቹን ሰባት ቴንብሮች ከፈረንሳይ ሀገር በማስመጣት ስራ ጀመረ።
 
በ1902 ዓ.ም ደግሞ ለውጭ ሀገራት አገልግሎት የሚውሉ ቴንብሮችን ወደገበያ አስገባ።
 
በዚህም አገልግሎቱን ከፍ አድርጎ በእግረኛ እና በፈረሰኛ የነበረው የፖስታ ስርጭት በተሽከርካሪዎች እንዲቀላጠፍ ፈጣንና ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት መስጠቱን ቀጠለ።
 
በስነ ጥበባዊ ስራዎቻቸው የሚታወቁት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የፖስታ ቴምብርን በመንደፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው።
 
ለኢትዮጵያ ፖስታ ፊላቴሊ ወይም ቴምብር ስብስብ ያበረከቱት አስተዋጾ ለኢትዮጵያ የበለፀገ የባህል ቅርስ እና ለመላው አፍሪካ አንድነት የነበራቸውን ፍቅር ያስተጋባል።
 
በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራቸው እርቀው ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የእናት ሀገራቸው ናፍቆት እንዳይበረታባቸው ትዝታቸውን በሽሮ በድርቆሽ በማር እና ቂቤ እንደቤተሰብ ሁኖም እያደረሰ ኖሯል፤ ዛሬም ያደርሳል።
 
ይህም አልበቃውምና በ2014 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት ተጨማሪ የአገልግሎት ውጥኖችን ይፋ አድርጓል ። ከእነዚህም መካከል የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አገልግሎት፣ ጥቅሎችን ቤት ለቤት ማድረስ እና ጭነቶችን በብትን መልኩ በአፍሪካ ሀገራት ማሰራጨት ይገኙበታል።
 
በቅርቡም ድርጅቱ በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ተቋማት ስኬት ሽልማት ከተበረከተላቸው አንዱ ለመሆን ችሏል።
 
የኢትዮጵያውያን የፖስታ ዘመን ሰዎች እንደ ብሔራዊ ቅርስ የሚቆጥሩት፤ በሺህ ትዝታዎች እና መንገዶች የታጀበው ድርጅት 130ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ይገኛል።
 
ተቋሙም በማኅበራዊ ትስስር ገፁ "130ኛ ዓመት የምስረታ በዓላችንን በኩራት አክብረናል። ይህ እረጅም ጉዟችን ፅናታችንን በሀገር ገፅታ ላይ የተጫወትነውን ሚና የሚያንፀባርቅ ነው። ለዚህ ታሪካችን ወሳኝ የሆኑ ሰራተኞቻችንን እና ደንበኞቻችንን እናመሰግናለን። ህዝባችንን በላቀ ሁኔታ ማገልገላችንን እንቀጥላለን" ብሏል።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top