ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያን ወደ ፈጣን ዕድገት እየመሯት ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል፡- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

4 Hrs Ago 61
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያን ወደ ፈጣን ዕድገት እየመሯት ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል፡- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ ወደ ፈጣን ዕድገት እየመሯት ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ተናገሩ፡፡
 
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው 3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ሊቀመንበሩ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያመጣች ያለው ለውጥ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
 
የአፍሪካ ሕዝብ ብዛት በ2050 ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይገመታል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ከዚህ ውስጥ ከ25 ዓመት በታች የሚሆነው 60 በመቶ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
 
አፍሪካ በየዓመቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሥራ ፈላጊዎች ቢኖሯትም፣ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለው ግን ከ3 ሚሊዮን ላልበለጠው እንደሆነ ነው ሊቀመንበሩ ያስታወሱት፡፡
 
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ እያመጣችው ያለው ለውጥ እጅግ አስደናቂ እና ለሌሎችም ማስተማሪያ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ ለአብነትም አዲስ አበባ ተለውጣ በጣም የምትገርም ከተማ የሆነችው በዚህ ጥረት ነው ብለዋል፡፡
 
"ባለፉት ሳምንታት በርካታ የአውሮፓ ከተሞችን አይቻለሁ፤ አዲስ አበባ ከነዚያ ከተሞችም የበለጠ ውብ ሆናለች፤ ሌሎች ከ56 በላይ የሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች በዚህ ለውጥ ሂደት ውስጥ ናቸው" ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ይህ የጠንካራ አመራር ውጤት ነው እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
 
"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ሀገር ታላቅ ሥራ እየሠሩ ናቸው፤ ወደ ግርብና ስንመጣ ኢትዮጵያ ከጤፍ ምርት በተጨማሪ ስንዴ፣ በቆሎ እና ሩዝ በስፋት አያመረተች ትገኛልች" በማለት ነው የኢትዮጵያን ፈጣን ለውጥ የገለጹት፡፡
 
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጋር ኢንዱስትሪዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች እየተመረቱ ያሉት ምርቶች በብዛትም በጥራትም እያደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከዚህ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡
 
አፍሪካ ለዓለም የምታበረክተው የሰው ኃይል ከ3 በመቶ የማይበልጥ ሲሆን፣ በአንጻሩ ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን 26 በመቶ ገደማ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ ይህን እውነታ ለመቀየር በፍጥነት መሥራት የሚገባው አሁን ነው ብለዋል፡፡
 
ግብርና ትልቁ የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጣሪ ዘርፍ መሆኑን ያነሱት ሊቀመንበሩ፤ የግል ዘርፉ እና በፍጥነት እያደገ ያለው የቴክኖሎጂ ዘርፍም የአፍሪካን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለመደገፍ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
 
በአፍሪካ በሥራ ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ አዳዲስ ትውልድ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህን አቅም ለአፍሪካ ዕድገት የሚጠቅም ለማድረግ በሁሉም ረገድ መደገፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top