የኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብር

3 Hrs Ago 58
የኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር በሪዮ ዴጄኔሮ ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
 
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና በማንኛውም ሁኔታ የማይለያዩ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋሮች መሆናቸውን እንደተናገሩ ሺንዋ ዘግቧል።
 
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በኮሙኒኬሽን፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በመሠረተ ልማት፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
 
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የባለብዙ ወገን ግንኙነትና ትብብር በማጠናከር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲያድግ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት መደረጉ ተመላክቷል።
 
ቻይና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ልማት ለምታደርገው የረጅም ጊዜ ድጋፍና እገዛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
 
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ በበኩላቸው፤ የቀጠናዊ ትብብር አካልና ቁልፍ ፕሮጀክት የሆነውን የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ለማጠናከር እንዲሁም የሁለትዮሽ ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነች ብለዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ እንደገለጹት፤ ቻይና እና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከመሰረቱ ከ55 ዓመታት ወዲህ ዓለም አቀፉ ሁኔታ ላይ የተለያየ ለውጥ ቢታይም ሁለቱ ሀገራት ምንጊዜም በቅንነትና በመደጋገፍ መዝለቅ ችለዋል።
 
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ትብብር በቻይና-አፍሪካ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ግንባር ቀደም ሆኖ መቆየቱንም አስታውቀዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብራዚል እየተካሄደ በሚገኘው የብሪክስ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛል።
 
በጌትነት ተስፋማርያም

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top