ሚካኤል አርቴታ ከአምስት አመት በፊት የማርቲን ኦዲጋርድ እና የአሌክሳንደር ይሳቅን ሁኔታ በሚከታተልበት ሰዓት ማርቲን ዙቢሜንዲ በሶሲዳድ ዋናውን ቡድን የተቀላቀለበት ጊዜ ነበር፡፡
በባስኩ ክለብ ራሱን በሚገባ ለማሳየት ጊዜ ያልወሰደበትን ማርቲን ዙቢሜንዲ ሁኔታ አርቴታ ባለፉት አራት እና ሶስት አመታት ሲከታተለው ቆይቷል፡፡
በ2023 የጥር ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ስፔናዊው አሰልጣኝ ሞይሰ ስካይሴዶን ከብራይተን ለማስፈረም ንግግር መጀመሩ ከመዘገቡ ፊት ዙቢሜንዲ ጋር ሰፋ ያሉ ድርድሮች እንደነበሩ የዘ አትሌቲኩ ጸሃፊ ጄምስ ማክኒኮላስ አስታውሷል፡፡

አማካዩ በሶሲዳድ መቆየትን ምርጫው ማድረጉን ተከትሎ አርሰናል ጆርጂኒሆን አስፈርሞ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ማርቲን ዙቢሜንዲ የዣቢ አሎንሶ አድናቂ ነው፡፡ የሚጫወትበት ቦታ፣ የጨዋታ መንገዱ እና ሌሎችም ጉዳዮች ከወቅቱ የማድሪድ አሰልጣኝ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ በእርግጥ አሎንሶ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ከመንገሱ በፊት ዙቢሜንዲ ከተገነበት ዙቢታ የሶሲደድ አካዳሚ አሳልፏል፡፡ ሪያል ሶሲዳድን ለረጅም ጊዜ በምክትል ፕሬዝደንትነት ያገለገሉት እና አርቴታንም፣ አሎንሶንም ዙቢሜንዲንም ከታዳጊነታቸው ጀምሮ ያሰለጠኑት ሮቤርቶ ሞንቴል የተባሉ ሰው አዲሱ የአርሰናል ኮከብ በአጨዋወት ከዣቢ አሎንሶ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በላሊጋው ከሚገኙ ምርጥ አማካዮች ከቀዳሚዎቹ አንዱ የሆነው ዙቢሜንዲ በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት በማድሪድ እና ሊቨርፑል በጥብቅ ሲፈለግ ቆይቷል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የአሎንሶ ማድሪድን መረከብ ዙቢሜንዲ ወደ ሎስ ብላንኮዎቹ እንዲያመራ ሊያደርገው ይችላል ቢባልም በመጨረሻም ከፈላጊው አርቴታ ጋር ተገናኝቷል፡፡
የሚገርመው የዙቢሜንዲ እና የአሎንሶ ወኪል ኢናኪ ኢባንዝ ይባላል፡፡ ሁለቱ የእግር ኳስ ሰዎች ተመሳሳይ ወኪል ኖሯቸው፣ በአንድ አካዳሚ አልፈው፣ ዙቢሜንዲም የአሎንሶ አድናቂ ሆኖ ስለምን አርሰናልን ምርጫው አደረገ ከተባለ የአንድሪያ ቤርታ የመደራደር አቅም እንዳለ ሆኖ ወኪሉ ኢናኪ ኢባንዝ የሚካኤር አርቴታ የቅርብ ወዳጅ መሆኑ ዝውውሩ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል፡፡
ለመሆኑ አርቴታ ይሄንን ያክል አመት ስለምን ሲከታተለው ቆየ?
ለ3ኛ ተከታታይ አመት በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል ዋንጫ ለማጣቱ በዋናነት የሚጠቀሰው ሁነኛ አጥቂ አለማግኘቱ ቀዳሚው ቢሆንም 6 ቁጥር ላይ በቋሚነት የሚያገለግል ትክክለኛ ሰው አለመያዙ ሌላው ምንክንያት ይሆናል፡፡
በእርግጥ እዚህ ቦታ ላይ ደክለን ራይስ የተሟላ ተጫዋች ነው ነገር ግን ይበልጥ ወደ ፊት ተጠግቶ ሲጫዎት ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን ማሳየቱ የማርቲን ዙቢሜንዲ መምጣት የመድፈኞቹን የአማካይ ክፍል ይበልጥ ጠጣር ያደርገዋል፡፡

ለማንችስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ዋንጫ ማንሳት ሮድሪ እና ፋቢኒሆ የነበራቸው ሚና ዋናው ጉዳይ መሆኑን የሚያነሳው የስካይ ስፖርቱ ጸሀፊ አሌክስ ኬብል አርሰናል ለአመታት ስድስት ቁጥር ላይ ለነበረበት ክፍተት ወሳኙን አማካይ ማግኘቱን አስቀምጧል፡፡ ለዚህ መሳያው ደግሞ በተጠናቀቀው የስፔን ላሊጋ የውድድር አመት ኳስ በማቀበልም፣ በማቋረጥም፣ የኳስ ሽግግሩ ላይ የነበረውን ቀጥተኛ ተሳትፎ መመልት በቂ ይሆናል፡፡
በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ሮድሪን ቀይሮ በገባበት 2ኛው አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴ እና ቡደኑ ጫና ሲፈጠርበት ኳስ የሚይዝበት እና የሚያረጋጋበት፣ በመከላካሉም በማጥቃቱም አጋዥ ሆኖ መገኝቱ ዙቢሜንዲ ለዚያ ቦታ የተፈጠረ ተጫዋች እንዲሆንም አድርጎታል፡፡

የቡድን ተጫዋች መሆኑ፣ የቴክኒክ ብቃቱ ፣ የጉዳት ታሪክ የሌለበት ሆኖ መገኘቱ እና ከምንም በላይ በሁለቱም እግሮቹ መጫዎት መቻሉ አርቴታ ለሚፈልገው ተለዋዋጭ የጨዋታ መንገድ ቀዳሚው ተመራጭ ሆኖ ኢምሬትስ ደርሷል፡፡
የአርሰናልን እንቆቅልሽ ለመፍታት ተስፋ የተጣለበት አዲሱ መድፈኛ ከደክለን ራይስ ጋር ከሚኖረው ጥምረት በተጨማሪ ማርቲን ኦዴጋርድ ያለውን የፈጠራ አቅም በነጻነት እንዲጠቀም የሚያደርገው ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የማርቲን ዙቢሜንዲ ዝውውር ከአርሰናል ጋር የተለያየውን ቶማስ ፓርቴን ለመተካት ብቻ የተደረገ ሳይሆን የጨዋታ መንገድን ጥራት የመጨመር ስለመሆኑ የባስኩ ተወላጅ የሶሲዳድ ቆይታ በቂ ማሳያ ነው፡፡
ያላባቸውን ክፍተት ለመሸፈን በዝወውሩ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት መድፈኞቹ ለአመታት የነበረባቸውን የአጥቂ ጉድለት ለመሙላት ደግሞ ከቪክቶር ጊዮኬሬሽ ጋር በግል ጉዳይ ስለመስማማታቸው ይፋ ሲሆን ዝውውሩ ከተጠናቀቀ የማርቲን ዙቢሜንዲን ሰሜን ለንደን መድረስ የተሟላ ሊያደርገው ይችላል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ