ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል፤አዳዲስ አባላት በመጨመራቸውም የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል ሲሉ ገልጸዋል።
አያይዘውም የጋራ ዓላማችን የበለጠ ይጠራል፤ አቅማችንም ይሰፋል ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሪዮ ዲ ጄኒሮ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የብሪክስ ጉባዔ የሰላም፣ የጸጥታ እና ዓለም አቀፍ አመራር መድረክ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
ስኬታማ ትብብርን ለማስቻል አጸፋዊ መተማመንን የሚያሳድጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመኖርን አጣዳፊነት በንግግራቸው አንስተዋል።
አክለውም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት ይረዳ ዘንድ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅራቸው ምሉዕነት ባለው መልክ የሚሻሻልበትን ሁኔታም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በይፋ ወደ ብሪክስ የተቀላቀለችው በ2015 ዓ.ም ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ፍትኃዊ የሆነ እኩልነት የሚሰፍንበት ብዝኃ ዋልታዊ ዓለምን ለመፍጠር ከሚተጉ ሀገራት ጋር በእኩል ደረጃ የተሰለፈችበት ስብስብ ነው።
እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ እንደምታደርግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡