ደቡብ ኮርያ ለኢትዮጵያ የህክምና ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አደረገች

4 Yrs Ago
ደቡብ ኮርያ ለኢትዮጵያ የህክምና ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አደረገች

የደቡብ ኮርያ መንግሥት ከአገሪቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚውሉ የህክምና ቁሳቁሶች እና የገንዘብ ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉ 28 ሺህ 33 የመመርመሪያ ኪቶች፣ 150 ሺህ 400 የፊት ጭንብል፣ 60 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮችን ያጠቃልላል።

ጎን ለጎንም ለኮሮናቫይረስ መከላከል የሚውል ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሁን ሚን ሊም እንደተናገሩት፤ የኮርያ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከኢትዮጵያ ጋር ይተባበራል።

ኮርያ በዓለም ደረጃ አሳሳቢ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የምታከናውናቸውን በጎ ተግባራትና ልምድ ለኢትዮጵያ ታካፍላለች ብለዋል።

በዚህ ላይ ያለውን አጋርነት በተለይም በኢንተርኔት በመታገዝ እንደምታጠናክር ገልጸው፤ በቀጣይም ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ድጋፍ በሚያስፈልጋት ሁሉ ኮርያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ድጋፉ በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ሥራ ያጠናክራል ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top