ቀይ መስቀል በአገራችን የፈተና ጊዜ የተወለደ እና የሰብዓዊነትን ፋይዳ በተግባር የተረጎመ ነው - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

4 Hrs Ago 77
ቀይ መስቀል በአገራችን የፈተና ጊዜ የተወለደ እና የሰብዓዊነትን ፋይዳ በተግባር የተረጎመ ነው - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ
 
ቀይ መስቀል በአገራችን የፈተና ጊዜ የተወለደ፣ ፈተናዎችንም የተረዳ እና የሰብዓዊነትን ፋይዳ በተግባር የተረጎመ ተቋም መሆኑን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኀበር 90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል መርሐ ግብር ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል አገራችን ችግር ውስጥ በገባችባቸው ወቅቶች ሁሉ ላከናወናቸው የሰብዓዊነት ተግባራት የኢትዮጵያ መንግስት ዕውቅና እንደሚሰጥ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተወረረችባቸው ወቅቶች የኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኀበር በጎ ፈቃደኞችና ሰራተኞች ለአገራችን የከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነትና የሰብአዊነት ተግባር፤ በጀግኖች አርበኞችና በመላው ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ታትሞ የቀረ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ቀይ መስቀል ሕዝባችንን በችግሩ ጊዜ ሲደርስለት የቆየ፤ የርህራሄና የበጎነት መገለጫ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ቅድመ አያቶቻችን በዓድዋ የጦር ሜዳ የቆሰሉ ወታደሮችን በመንከባከብ ያሳዩት የሞራል ልዕልና የማኀበሩ መሰረት ሆኖ አሁንም ድረስ ጎልቶ እንደሚታይ አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ሰራተኞችም ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው ለፈጸሙት የሰብዓዊነት ተግባር ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።
በቀጣይም የማኀበሩን የትኩረት አቅጣጫ በዘላቂነት እራስን መቻል ላይ እንዲመሰረት ማድረግ ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል።
ማኀበሩን ከእርዳታ በማላቀቅ የሰብዓዊ ተግባራትን በራስ አቅም ለመፈጸም የሚያስችል ግብ መንደፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ማኀበሩ 100ኛ ዓመቱን ሲያከብር በገንዘብና በዕውቀት እራሱን ችሎ የዘመነ ደንብና አዋጅ አበጅቶ፤ በቀጣናው እንዲሁም በአፍሪካ የሰብዓዊነት ተምሳሌት ሆኖ ማየት እንፈልጋለን ብለዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top