በዚህ ሰዓት ስልክዎን ወይም ኮምፒውተርዎን እያዩ ነው? እስቲ ለአፍታ ያቁሙ እና አቀማመጥዎን ይገምግሙ፤ ስልክዎን እና ኮምፒተርዎን የሚመለከቱት አቀርቅረው ነው? መልስዎ አዎ ከሆነ አንገትዎ ላይ ከባድ ሸክም ጭነዋል።
ማዮ ክሊኒክ ላይ በወጣ ጥናት መሰረት በርካታ ሰዎች በየቀኑ በአማካይ 3 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ስልካቸው ላይ የሚያሳልፉ ሲሆን፣ በቀን ውስጥ ቢያንስ ለ58 ጊዜ ስልኮቻቸውን ይመለከታሉ።
በአሜሪካ ግማሽ ያህሉ ነዋሪዎች በየቀኑ በአማካይ ከ4 እስከ 5 ሰዓት ከተንቀሳቃሽ ስልካቸው ጋር እንደሚያሳልፉ ተገልጿል።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በሥራ ምክንያት በቀን ለ8 ሰዓታት ያክል ከኮምፒውተር ጋር የሚያሳልፉ ሲሆን፣ ከሥራ በኋላ ደግሞ ቢያንስ በቤታቸው ከ2 እስከ 4 ሰዓታት ከኮምፒውተር ወይም ከስልካቸው ጋር ሊያሳልፉ ይችላሉ።
ችግሩ ታዲያ ኮምፒውተር እና ስልክ በመጠቀም የሚያሳልፉት ጊዜ በአንገታቸው እና በሰውነታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ብሎም ለአንገት መታጠፍ እና የጀርባ ሕመም የሚዳርጋቸው መሆኑ ነው።
ተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ታብሌት ለመመልከት በ45 ዲግሪ ጭንቅላታችንን ወደፊት ስናዘነብል የአንገት መጣመም 'ቴክ ኔክ' ወይም 'ቴክስት ኔክ' በመባል የሚታወቀው የአንገት ሕመም የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ነው በጥናቱ ተመላክቷል።
በዚህ ሁኔታ አንገታችንን አዘንብለን ስንሠራ በአንገታችን፣ በትከሻችን እና በጀርባችን ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማነጻጸር አንድ ጋሎን (3.8 ሊትር) ፈሳሽ አንገታችን ላይ አስረን ማየቱ በቂ ነው ይላል ጥናቱ።
ይህ ማለት ከጭንቅላታችን ክብደት በተጨማሪ ወደ አራት ኪሎ ግራም ተጨማሪ ክብደት ለተጠቀሰው ጊዜ ያክል በአንገታችን ተሸክመን መቆየት እንደ ማለት ነው፡፡
አንገታችንን ዝቅ አድርገን እነዚህን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ለረጅም ጊዜ እየተጠቀምን በቆየን ቁጥር ታዲያ በአንገታችን እና በጀርባችን የኋላ ጡንቻ ላይ የሚፈጠረው ጫና በሂደት ለአንገት መታጠፍ የሚዳርግ ነው።
በዚህም ምክንያት በንግድ፣ በትምህርት ቤቶች እና በኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚገኙ እና ሥራዎቻቸው ከስልክ እና ኮምፒውተር ጋር የተገናኘ ሰዎች የአንገት መታጠፍ (“tech neck") የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
እንደጥናቱ በአሁኑ ጊዜ የአንገት ሕመም ለአካል ጉዳት ምክንያት በመሆን በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በየዓመቱ ከ30 በመቶ በላይ ሰዎች ለዚህ ችግር እየተዳረጉ ይገኛሉ።
አብዛኛዎቹ የአንገት ሕመም የሚጋጥማቸው ሰዎች በሕክምናም ሆነ ያለ ሕክምና መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ ቢሆንም 50 በመቶ በሚጠጉት ላይ ግን ዘላቂ ሕመም እና ችግር ጥሎ እንደሚያልፍ ነው ጥናቱ ያስቀመጠው።
ችግሩ የሚፈጠረው ስልክ እና ኮምፒውተር ላይ ስንሠራ አንገታችንን ወደ ታች ዝቅ በማድረግ ብቻ ሳይሆን እንዲታየን ቀረብ በማድረግ እና ለረጅም ጊዜ በአንድ ዓይነት አቀማመጥ ሆነን ስንሠራም ጭምር ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ልማድ ችግር የሚያስከትለው በአንገት ላይ ብቻ ሳይሆን በጀርባችን አከርካሪ ላይም ጭምር ሆኖ ለራስ ምታትም ጭምር ምክንያት እንደሚሆን ነው የተጠቀሰው።
ይህ ችግር በልጆች ላይ በፍጥነት የማይታይ ቢሆንም ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ግን በሰውነታቸው ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ነው የሚነገረው።
በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ለረጅም ጊዜ ኮምፒውተር እና ስልክ ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ላይ ጥንቃቄ ካላደረጉ የጡንቻ ድካም፣ ውጥረት እና ጭንቀት ሊከሰትባቸው ስለሚችል ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ በማድረግ እና ቦታ በመቀያየር ውጥረቱን ማቃለል እንዳለባቸው ይመከራል።
👉🏾የኮምፒውተር እና ስልክ ስክሪኖችን ከዓይናችንን ከ20 እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ማራቅ፤
👉🏾የኮምፒውተራችንን ስክሪን ከፍታ በማስተካከል መጠቀም፤ ይህ ማለት የምናነባቸውን ፊደላት በ15 ዲግሪ ለማየት ዓይናችን ከኮምፒውተሩ ሞኒተር አንጻር ከግማሽ እስከ አንድ ከግማሽ ኢንች ከፍ ሊል ይገባል ማለት ነው፤
👉🏾ተቀምጠን ስንሠራ ጭንቅላታችንን እና ጀርባችንን ማናበብ እና ምቾት እንዲሰማን ማድረግ፤
👉🏾ስንሠራ እጆቻችንን ቀጥ ማድረግ እና ክርኖቻችንን ደግሞ እስከ 90 ዲግሪ ማጠፍ፤
👉🏾ጉልበታችንን ስናጥፍ ከወገባችን እና ከእግራችን ጋር ማናበብ፤
ይህን ችግር ለመከላከል የሚረዱን ዘዴዎች እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ኮውምፒውተር ላይ ስንሠራ ቀጥ ብለን ወደ ፊት ስንመለከት አንገታችን፣ ጀርባችን እና ትከሻችን ላይ ያሉ ጡንቻዎች ዘና ለማለት አጋጣሚ ያገኛሉ፤ ይህም አላስፈላጊ ጫና በነርቮቻችን ላይ እንዳይከሰት ይከላከላል።
ይህ ማለት ጆሮአችን በትከሻችን ትይዩ እንዲሁም ትከሻችን በወገባች ትክክል ቀጥ በማድረግ ራሳችንን ቀና በማድረግ ማለት ነው።
በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ አንድ ቦታ ተቀምጠን ስንሠራ ከቆየን በኋላ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች ማመቻቸት የአንገት መጣመምን እና ተያያዥ ችግሮችን ለማስወገድ ይረዳናል።
በለሚ ታደሰ