የፌዴራል እና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎበኙ

31 Days Ago
የፌዴራል እና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎበኙ

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ የሚከናወነውን የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል::

በጉብኝቱ ወቅት ማብራሪያ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የልማት ኮሪደር ስራዎቹ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ ከማድረግ በተጨማሪ ከተማዋን የሚመጥን የመንገድ፣ የመብራት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት፣ ምቹ የእግረኛ መንገድ እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎችን ያካተተ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ የልማት ስራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፊ የኮሪዶሮች ጥናት በማድረግ የተጀመረው ይህ የልማት ኮሪደር በአምስት ኮሪደሮች ተለይቶ ግንባታው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ከንቲባዋ፤ አካባቢዎችን ማልማት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡንም ተጠቃሚ በማድረግ ሰፊ ስራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ እና ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ቅንጅት የታየበት ስራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ የልማት ኮሪደር ስራውን ሲተገብር ቅድሚያ ለሰው በማለት ከነበሩበት ጎስቋላ የመኖሪያ አካባቢ በማስወጣት በመንግስት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ጽዱ እና ለመኖር ምቹ የሆኑ የመኖሪያ ቤቶችን ተገንብተው እንዲረከቡ መደረጉን መግለፃቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአንፃሩ የንግድና የመስሪያ ቦታ ለነበራቸው በተገቢ ቦታ የተሻለ የንግድ ቦታ መሰጠቱን እንዲሁም የግል ይዞታ ለነበራቸው የካሳ፣ ምትክ ቦታ ፣ የማጓጓዣ እንዲሁም ቤት እስኪገነቡ ድረስ የቤት ኪራይ ክፍያ በማሟላት የልማት ስራው በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት አመራሮቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየሰራቸው ያሉ ስራዎች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን እና ልማት መገንባት ብቻ ሳይሆን ነዋሪውን አካትቶ ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን በሚገባ የሚያሳይ ስራ መሰራቱን መመልከታቸን ገልጸዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top