"ዓለም ተጨማሪ ጦርነት መሸከም አትችልም" - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

1 Mon Ago 345
"ዓለም ተጨማሪ ጦርነት መሸከም አትችልም" - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

መካከለኛ ምስራቅም ይሁን ዓለም ተጨማሪ ጦርነት መሸከም የሚችሉበት አቅም የላቸውም ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናገሩ፡፡

ኢራን በደማስቆ በሚገኘው የቆንስላ ፅህፈት ቤቷ ላይ ለተቃጣባት ጥቃት ቅዳሜ ሌሊት እስራኤል ላይ በሰነዘረችው አፀፋዊ ምላሽ 300 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን መላኳን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት መንገሱ ተገልጿል፡፡

የኢራንን ጥቃት ተከትሎ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ሰላም ስጋት የገባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በትናትናው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል፡፡

በዚህ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና በአስፈሪ ጦርነት አፋፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመካከለኛ ምስራቅ ቀጣናም ይሁን ዓለም ተጨማሪ ጦርነት መሸከም የሚችሉበት አቅም የላቸውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በቀጠናቀው ሀገራት የሚገኘው ህዝብ በከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ እና በእስራኤልና ኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ውጥረት ለቀጠናው እና ለዓለም ስጋት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ፀሃፊው፤ ሀገራቱ ከገቡበት ውጥረት ለመውጣት ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች መታቀብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አክለውም፤ አስራኤል እና አጋሮቿ ኢራን ላይ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ውጥረቱን የበለጠ ከማባባስ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡

በእስራኤል እና ኢራን መካከል እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ውጥረት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት እና ስጋት መፍጠሩን የዘገበው ቲአርቲ ወርልድ ነው፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top