የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከጀርመን ኩባንያ ጋር የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ

13 Days Ago
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከጀርመን ኩባንያ ጋር የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከጀርመን የስራ እድል ፈጠራ ማስተባበሪያ (አይ ኤፍ ኢ) ጋር የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ።
 
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ፤ የጀርመኑ ማስተባበሪያ ቢሮ ኮርፖሬሽኑ የያዘውንና ግዙፍ ሀገራዊ አላማ የሆኑትን የስራ እድል ፈጠራን መጨመር፣ የውሀ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአምራች ኩባንያዎች አቅም ማሳደግና እርካታን ለመጨመር በመተባበር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ኮርፖሬሽኑም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ግዜ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅም ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጠዋል።
 
ስምምነቱ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የንፁህ ውሀ አቅርቦትን ለማሳደግ፤የአምራች ኩባንያዎችን እርካታ በመጨመር ፓርኩ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ እና ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ነውም ተብሏል።
 
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሐይለሚካኤል፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እንዲሁም የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና እድገት ሚኒስትር ማስተባበሪያ ዶክተር ዶሚኒካ ፕሪይዚንግን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎች መገኘታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top