የመጀመሪያዎቹ ኤምባሲዎች በአዲስ አበባ

1 Mon Ago 354
የመጀመሪያዎቹ ኤምባሲዎች በአዲስ አበባ

ሀገራት ከሌላ ሀገር ጋር ለሚኖራቸው የባህል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ኢምባሲዎችን ይከፍታሉ፡፡

በኢትዮጵያም ቢሆን ኢምባሲያቸውን በመዲናችን አዲስ አበባ የሚከፍቱ ሀገራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ያደረገችው አስዋጽኦ ላቅ ያለ ነው፤ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ባለመገዛቷ ምክንያት  ለተቀረው የአፍሪካ ህዝብ ነጻ መውጣት አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡

ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገበችው አኩሪ ድል ከሌሎች ሀገራት ጋር ለምትፈጥረው ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ጥሎላታል፡፡ 

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ ፈጣንና ሰፊ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን አከናውናለች፡፡

ኢምባሲያዎች መከፈታቸው ለአንድ ሀገር ያለው ጠቀሜታ የጎላ ሲሆን በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከተለያዩ የአለም ሀገራት ጋር ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ስታከናውን ቆይታለች፡፡

በአለም ላይ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት እውቅና ከሰጣቸው 195 ሀገራት ውስጥ 134 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ኢምባሲያቸው በመክፈት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ሁለትዮሽ ግንኙነት እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአብዛኛው የአለም ሀገራት ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት እንዳላት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ 134 ሀገራት ኤምባሲያቸውን ከፍተው እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድዔታ ብርቱካን አያኖ ሚያዝያ ወር ላይ በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ 134 ሀገራት በኢትዮጵያ ኢምባሲያቸውን መክፈታቸውን አብራርተው ይህም አዲስ አበባ የድምሎማሲ ማዕከል መሆኗን ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

ሚኒስትር ድዔታዋ አክለውም የከተማዋን አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት በማስፋት ኢትዮጵያ እንደሀገር የሚጠበቅባትን ሀላፊነት በመወጣት ሃገሪቱ የአለማቀፍ ድፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ዘመናትን የተሻገረ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ለማሳያነትም ንግስት ሳባ ከክርስቶስ ልደት 1000 አመት በፊት የነገሰች እነደነበር ይታወቃል፡፡

ንግስት ሳባ የእስራዔልን ንጉስ ሰለሞንን ለመጎብኘት ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገችው ጉዞ በታሪክ የመጀመሪያው ይፋዊ የመሪዎች ጉዞ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ 

ንጉስ ሰለሞን ለንግስቲቱ በቤተመንግስት ያደረገው አቀባበልና የዴር ሱልጣንን ገዳም በስጦታ ማበርከቱ በበጎ ይወሰዳል፡፡

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያና የእስራዔልን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከሶስት ሺህ አመታት በላይ ያስቆጠረ ነው አስብሎታል፡፡

ከዚያ በኋላም ቢሆን በየዘመናቱ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአለም ሀገራት ጋር ሰፊ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ስታከናውን ቆይታለች፡፡

ነገርግን በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ ፈጣንና ሰፊ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን አከናውናለች፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በአድዋ ድል ያስመዘገበችው አኩሪ ድል ከሌሎች ሀገራት ጋር ለምትፈጥረው ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ጥሎላታል፡፡ 

ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ከጀመረችባቸው ሀገራት መካከል አምስቱን ቀዳሚ ሀገራት እንመለከታለን፡፡

 

1/ ኢጣሊያ

ኢጣሊያ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢምባሲዋን በመዲናችን አዲስ አበባ የከፈተች የመጀመሪያዋ ሀገር ናት፡፡

ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት መፍጠር የጀመረችው በ1869 ዓ.ም በኦራዚዮ አንቲኖሪ የሚመራ የመልክዓ ምድር አጥኚ ቡድን በላከችበት ወቅት ነበር፡፡

ይሁን እንጅ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ድፕሎማሲያዊ ቅርጽ የያዘው በ1875 ዓ.ም በፔትሮ አንቶኔሊ የተመራ ልዑክ ወደኢትዮጵያ በተላከበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአድዋ ጦርነት ምክንያት ሻክሮ ቆይቷል፡፡

በመጨረሻም ጣሊያን በጦርነቱ ማግስት አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ በወራት ውስጥ በ1888 ዓ.ም የመጀመሪያውን የኢጣሊያ ቆንጽላ በአዲስ አበባ በመክፈት ግንኙነቷ ለማደስ ጥረት አድርጋለች፡፡

አምባሳደር ቺኮድላኮላ ደግሞ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተደርገው የተሸሙ የመጀመሪያው ለመሆን በቅተዋል፡፡

 ጣሊያን ምንም እንኳን ሁለተኛ ዙር ወረራ ፈጽማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ላፉት 128 አመታት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማስቀጠል ችላለች፡፡

በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪክም ረጅም እድሜ ያስቆጠረች ሀገር ናት፡፡

 

2/ አሜሪካ   

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መደበኛ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድመሰረት ንግግር የተጀመረው በ1839 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል፡፡

በመጨረሻም ግንኙነቱ ድፕሎማሲያዊ ቅርጽ እንዲኖረው የተደረገው በሮበርት እስኪነር የተመራ የልዑካን ቡድን በ1896 ዓ.ም ኢትዮጵያን እንድጎበኝ ከተደረገ በኋላ በተፈጸመ ውል መሆኑን የድፕሎማቲክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

በመሆኑም ከሁለት አመት በኋላ ማለትም በ1898 ዓ.ም አሜሪካ የመጀመሪያውን ቆንስላ ጽ/ቤቷን አዲስ አበባ ውስጥ በመክፈት ሁለቱ ሀገራት ይፋዊ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ጀመሩ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለፉት 118 አመታት መዝለቅ ችሏል፡፡

 

3/ እንግሊዝ

በተለይ ከአድዋ ጦርነት በኋላ ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ ሀገራት በአዲስ አበባ ኢምባሲያቸውን ለመክፈት ብዙ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ በዋናነት የምትጠቀሰው ደግሞ እንግሊዝ ናት፤ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት የጀመረችው ጄምስ ብሩዝ የተባለው ስኮትላንዳዊ በ1722 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት ባደረገበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በ1802 የእንግሊዝ መንግስት መልዕክተኛ የነበረው ሄንሪ ሶልትን ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ቢሆንም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ግን ይፋዊ ሁኖ አልተጀመረም፡፡

በ1860 ዓ.ም እንግሊዞች ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በነበረው ጦርነት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ተቀዛቅዞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ይሁንእንጂ የአጼ ምኒልክን ወደስልጣን መምጣት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ይፋዊ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አዲስ ጀመረ፡፡ እንግሊዝ በ1899 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያዋን ቆንስላዋ ጽ/ቤት ከፈተች፡፡ በዚሁ ወቅት ጆን ሃሪንግተን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የእንግሊዝ አምባሳደር ተደርገው በይፋ ስራቸውን ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያና እንግሊዝ የ117 አመታት ድፕሎማሲያ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡

 

4/ ፈረንሳይ

እንደሌሎቹ የአውሮፓ ሀገራት ወደኢትዮጵያ መምጣት የጀመረችው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነበር፡፡ ነገርግን ሀገሪቱ በይፋ ቆንስላ ከፍታ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመረችው ከእንግሊዝ ጋር በተመሳሳይ አመት ነበር፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ በ1899 ዓ.ም፡፡   በወቅቱ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር የነበሩት ደግሞ ሌኦንስ ላጋርድ ነበር፡፡ ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 117 አመታት ድፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማስቀጠል ችለዋል፡፡

 

5/ ሩሲያ   

የኢትዮጵያና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የአሁኗ ሩሲያ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቢሆንም በአጼ ዮሃንስ ዘመነ መንግስ ወደተሸለ ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡

በአጼ ምኒልክ የአስተዳደር ዘመን በ1881 ከራሺያ በመጣ የልዑካን ቡድን እንድሁም በ1887 ከኢትዮጵያ በተላከ የልዑካን ቡድን አማካኝት የተለያዩ የመልዕክት ልውውጦች ተካሂደው ነበር፡፡

በመጨረሻም ሩሲያ በአዲስ አበባ የመጀመሪያውን ኢምባሲዋን በ1902 ዓ.ም እንደመሰረተች ይነገራል፡፡ ሩሲያ በኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ሳይሆን ቋሚ ኢምባሲ የከፈተች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትጵያ  እና ሩሲያ ላለፉት 114 አመታት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማስቀጠል ችለዋል፡፡

 

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top