በዓዲግራት ከተማ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው

3 Mons Ago
በዓዲግራት ከተማ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው
ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ12 የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የዓዲግራት ከተማ አስተዳደር ገለጸ።
 
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ እየተከናወነ ያለው የከተማዋ አስተዳደር በመደበው 351 ሚሊዮን ብር እና የዓለም ባንክ ባደረገው የ300 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሆኑም ተጠቅሷል።
 
የዓዲግራት ከተማ ከንቲባ አቶ ሰሎሞን ሐጎስ እንደገለፁት፣ የልማት ፕሮጀክቶቹ ከያዝነው ጥር ወር መጀመሪያ ጀምሮ እየተከናወኑ ያሉ ናቸው።
 
ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል የሁለት ኪሎ ሜትር የአስፋልት ማንጠፍ ስራ እንዲሁም 8 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትርን ለሚሸፍን የውስጥ ለውስጥ መንገድ የኮብል ስቶን እና ጠጠር የማልበስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በክረምት ወቅት የሚያጋጥመውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የሰባት ኪሎ ሜትር የውሃ ማፋሰሻ ፣የእግረኞች እና የተሽከርካሪዎች መሸጋገርያ ድልድይ ግንባታም መጀመሩን አስታውቀዋል።
 
በከተማው የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሻሻል የ17 ኪሎ ሜትር የውኃ መስመር ቁፋሮ እና የቱቦ ቀበራ እንዲሁም የ20 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ስራም ከፕሮጀክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።
 
የልማት ፕሮጀክቶቹ ለ650 ወጣቶች የሥራ ዕድልን እንደፈጠሩ ጠቅሰው፤ ከነዚህ ውስጥም 374ቱ ሴቶች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የልማት ፕሮጀክቶቹ አስተባባሪ አቶ ተክላይ ግርማይ ናቸው።
 
"ከጦርነት ድባብ ወጥተን ወደ ሰላምና ልማት በመግባታችን ደስተኞች ነን" ያለው በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ኪዳነ ገብረዮሃንስ ነው።
 
''የሰላም እና የልማት መንገዱ ዘላቂ ከሆነልን ራሳችንና ቤተሰቦቻችንን ብቻ ሳይሆን አካባቢያችንን መልሰን ለማልማት ዝግጁ ነን'' ብሏል ወጣቱ።
ወጣት ሳምሶን ብርሃነ በበኩሉ፤ ወጣቶች ሰርተን ለመለወጥ በምናደርገው ጥረት የሌሎች በጎ ድጋፍ አስፈላጊ ነው ብሏል።
 
የልማት ፕሮጀክቶቹ የፊታችን ሰኔ ወር 2016 ዓ/ም ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ መገለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top