"በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ባቀድኩት ልክ እንዳልሰራ አድርጎኛል" - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

3 Mons Ago
"በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ባቀድኩት ልክ እንዳልሰራ አድርጎኛል" - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ሁኔታ እና የሰላም መደፍረሶች ምክንያት ስራውን በእቅዱ መሰረት እያከናወነ አለመሆኑን የኢትዮጲያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለፀ፡፡

ከኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጲያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው የስራ ቆይታው በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ እንደ አዲስ የተቋቋመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለስራው የሚያስፈልጉ የአቅም ግንባታዎች መሰራታቸውን የጠቀሱት አቶ ጥበቡ፤ የተቋሙን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን እና ተሳታፊዎችን የመለየት ስራም መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ምክክሩ ሀገራዊ እንዲሆን ከተፈለገ በዋናነት ህብረተሰቡ ጉዳዩን በደንብ ሊረዳው ይገባል ያሉት አቶ ጥበቡ፤ ህብረተሰቡን የማንቃት እና የማስገንዘብ ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡

ኮሚሽኑ የተለያዩ ስራዎችን አቅዶ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ እቅዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ፈታኝ የሆኑ ነገሮች እንደገጠሙት ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ እና የሰላም መደፍረስ ኮሚሽኑ ባቀደው ልክ እንዳይሰራ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡

ምክክሩ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ያስፈለገው የሀሳብ ልዩነቶችን ወደ ግጭት እንዳይሄዱ ለማድረግ ነው ያሉት አቶ ጥበቡ፤ ምክክሩን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ግን አንጻራዊ ሰላም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ምክክሩ የመላውን ህብረተሠብ እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚፈልግ ቢሆንም በየአካባቢው ያሉ የጸጥታ ሁኔታዎች ኮሚሽኑ ስራውን በእቅዱ መሰረት እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበታል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

ምንም እንኳን ስራዎችን በተገቢው ሁኔታ ለማከናወን ፈተናዎች ቢገጥሙም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በስፋት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰላም እጦት ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሰላም የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማምጣት ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር አብሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝም አቶ ጥበቡ ጠቅሰዋል፡፡

በተስሊም ሙሀመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top