"በስንዴ ራሳችንን መቻላችን ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድል ነው" - ዶ/ር ብርሀኑ ሌንጂሶ

3 Mons Ago
"በስንዴ ራሳችንን መቻላችን ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድል ነው" - ዶ/ር ብርሀኑ ሌንጂሶ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ውስጣዊ የሆነ የፖለቲካ ልዩነትን ማራመድ ትክክል አይደለም ሲሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት፣ በሮም ጣልያን በተሰናዳ ክብረ በዓል የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ መሸለማቸው ይታወሳል።

ሽልማቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) በስንዴ ራሳችንን መቻላችን ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አረንጎዴ አሻራ፣ የሌማት ቱርፋት፣ እና የገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች በምሳሌነት እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን እንድትችል የተሰራው ስራ የተለየ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሀገሪቱ በስንዴ ጉዳይ ከውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት እንደነበረባት አንስተዋል፡፡

በዚህም የስንዴ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ ጣልቃ ገባነትን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እዚህ ላይ የሰጡት አመራር የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ይሄንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት የፋኦ አግሪኮላ ሽልማት ትክክለኛ እና የሚገባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብሄራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ውስጣዊ የሆነ የፖለቲካ ልዩነትን መጠቀም ትክክል አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ብሄራዊ ጥቅምን ሊያስከብሩ የሚችሉ ጉዳዬች ላይ ያልተገቡ ነገሮችን ማድረግ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሽልማቱ ለሌሎች ስራዎች መንደርደሪያ የሆነ እና ከዚህ የበለጠ እንድንሰራ የሚያደርገን ነው ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

በተስሊም ሙሀመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top