የዓድዋ ድል በመደመር እሳቤ ለአፍሪካ እና ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ የሆንበት ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው - ዶክተር አለሙ ስሜ

2 Mons Ago
የዓድዋ ድል በመደመር እሳቤ ለአፍሪካ እና ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ የሆንበት ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው - ዶክተር አለሙ ስሜ

የዓድዋ ድል በመደመር እሳቤ ለአፍሪካ እና ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ የሆንበት ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገለጹ።

"ዓድዋ የመደመር ተምሳሌታዊ አርማ" በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ በአዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ የዓድዋን የድል ቀን ስናከበር ጀግኖች አባቶችና እናቶች የፈፀሙትን ታላቅ ገድል በመዘከር ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል መላ ኢትዮጵያውያን በህብርና በመደመር ለሀገራቸው ክብር ገድል የፈጸሙበት ተምሳሌታዊ ድል መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ያለምንም ልዩነት በአንድነት ቆመው የማይቻል የሚመስለውን ሃይል በፅናት ታግለው በማሸነት የጀግንነት ገድል ፈፅመዋል ብለዋል።

የዓድዋ ድል በአንድነት የተገኘ የድል ብስራት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የዚህ ዘመን የመደመር ተምሳሌት ሆኖ ሁላችንም ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ መቆም አለብን ነው ያሉት።

የዓድዋ ድል በመደመር እሳቤ ከሀገር አልፎ ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ፋና ወጊ መሆን የቻልንበት ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል በመደመር የተገኘ ገድልና የዚህ ዘመን የመደመር ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ዘመንም ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በጋራ ለሀገር አንድነት፣ ክብርና ልዕልና መሰለፍን የሚያስተምር እንደሆነም አንስተዋል።

የአሁኑ ትውልድ ከውስጥና ከውጭ በነጠላ ትርክት፣ በድህነትና ጦርነት የሚፈታተኑትን ተግዳሮቶች በአልበገር ባይነት ማሸነፍ እንዲችል ከአድዋ መማር አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

ከፍታችንን ማፅናት የሚያስችሉ ተምሳሌቶችን በመውሰድ ውስጣዊ አንድነትን ከሚሸረሽሩ ጉዳዮች በመራቅ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዚህ ዘመን ዓድዋ ድህነትን ማሸነፍ፣ አብሮነትን ማፅናት፣ በሀሳብ ልዕልና ሀገርን መገንባት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

ከቅድመ አያቶች የወረስነውን ታሪክ በዚህ ዘመን አውድ ለመድገም ቴክኖሎጂን መታጠቅ፣ ጠንክሮ መስራት፣ ሌብነትን መታገልና አሰባሳቢ ትርክቶችን መገንባት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የጸረ-ድህነት፣ የኅብረ ብሔራዊነትና የመከባበር አርበኛ እንሁን ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው የዓድዋ ድል የመደመር ማንፀሪያና የዚህ ዘመን የመሰባሰቢያ ትርክት መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል በቀደምት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የተገኘ አኩሪ ድልና የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ መሆኑንም አክለዋል።

ኢዜአ የፓናል ውይይቱን ያዘጋጀውም የኢትዮጵያውያንን የትላንት ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚና ዛሬም በመደመር እሳቤ ለመድገም መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በህብረ ብሔራዊ አንድነት በመሰለፍ ወራሪን ያሸነፉበት የመደመር ተምሳሌታዊ አርማ መሆኑንም ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top