የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ የተሰኘው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን በትውልድ ቅብብሎሽ ለብሔራዊ ጥቅሞቻቸው በጋራ እንዲቆሙ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው - ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ

2 Mons Ago
የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ የተሰኘው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን በትውልድ ቅብብሎሽ ለብሔራዊ ጥቅሞቻቸው በጋራ እንዲቆሙ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው - ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከአዲስ ዋልታ እንዲሁም ከአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ጋር በጋራ ያዘጋጁት "የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ" መጽሐፍ በዛሬው ዕለት በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ተመርቋል።

መጽሐፉ መጻኢ ዕድልን ለመወሰን ፈተናን ለመሻገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፤ የዓባይ ወንዝ እና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ጂኦ-ፖለቲካ እና ብሔራዊ ደኅንነት በመወሰን ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተጠቁሟል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ወቅት፥ መጽሐፉ ኢትዮጵያ በታሪክ የባህር በር ያጣችበትን ሁኔታ እንደሚዳስስ ጠቁመው፤ ለኢትዮጵያ ነባራዊ ፍላጎት መፍትሄ የሚያመላክት ስለመሆኑም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፥ መጽሐፉ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለመድረስ የምታደርገው ጥረት የዜጎች የጋራ ስራ ምን መሆን እንዳለበት ያመላክታል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የአባይ ተፋሰስ እና የቀይ ባህርን ቀጣናን የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አድርገው እንደሚመለከቱ መጽሐፉ አጽንኦት ሰጥቶ መዳሰሱንም ተናግረዋል።

የባህር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ወሳኝ ስትራቴጂዎችን እንደሚያትትም ጠቁመዋል።

የአዲስ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሀመድ ሀሰን፥ ትውልዱ ስለሁለቱ ውሃዎች እንዲያውቅ፣ እንዲማርና እንዲመራመር መጽሐፉ ስትራቴጂያዊ መንገዶችን ያመላክታል ብለዋል።

በሁለቱ ውሃዎች ጉዳይ ልሂቃን እንዲወያዩበት፣ አጥኚዎችም እንዲያብራሩትና ትውልዱ በእውቀት እንዲሰራበት መጽሐፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንድሚያበረክትም ጠቁመዋል።

አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለትውልዱ አሻራ ለመጣል ከተባባሪ አካላት ጋር ይሰራል ያሉት ደግሞ የቤተ-መጻሕፍቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ ናቸው።

ትውልዱ የተሰጠውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ እንዲጠቀም እና ለመጪው ጊዜ ደግሞ ራዕይ አንግቦ እንዲሰራ አቅጣጫ ለማመላከት መጽሐፉ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

መጽሐፉ ስድስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስና በሌሎች ዘርፎች ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ምሁራን ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ተነግሯል።

በመጽሐፍ ምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ መረጃ በማቅረብና በታላላቅ ሚዲያዎች ላይ ማብራሪያ በመስጠት የሚታወቁት መሀመድ አልአሩሲ እና ዑዝታዝ ጀማል በሽር “የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ” የክብር አምባሳደርነት ተሰጥቷቸዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top