የጥንታዊውን ሰው ጉዞ የሚያመለክት አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝት ይፋ ሆነ

1 Mon Ago
የጥንታዊውን ሰው ጉዞ  የሚያመለክት አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝት ይፋ ሆነ
ጥንታዊ ሰው ከአፍሪካ ወደ ሌሎች አህጉራት ወንዞችን እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም እንደተጓዘ ጥናት ሲያካሂድ የቆየው የተመራማሪዎች ቡድን ይፋ አደረገ።
 
አጥኚ ቡድኑ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሽንፋ እና መተማ ረባዳ ቦታዎች ሲያካሂድ የቆየውን የጥናት ውጤት ነው ይፋ ያደረገው።
 
ጥንታዊ ሰው ከአፍሪካ ወደ ሌሎች አህጉራት የተጓዘው ለምለምና በዛፍ የተሸፈነ መሬትን ተከትሎ ሳይሆን፤ ደረቅ የአየር ንብረትን ተቋቁሞ ወንዞችን እንደ መሻገሪያ በመጠቀም መሆኑን ቡድኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
 
ይህም ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን፤ ዘመናዊ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሞቃታማ የአየር ንብረትን ተቋቁሞ ከአፍሪካ ወደ ዓረቡ ዓለም እና አዉሮፓ መሻገሩን የሚያሳይ የመጀመሪያ የሳይንስ ግኝት መካነ ቅርስ እንድትሆን ያስችላታል ነው የተባለው።
 
ጥናትና ምርምሩን ያደረጉት የአዲስ አበባ እና ቴክሳስ ሂውስተን ዩንቨርሲቲ ምሁራን ሲሆኑ፤ የምርምርና ጥናት ቡድኑ መሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሰሃ የጥናቱን ውጤቱን ይፋ አድርገዋል።
 
የምርምር ግኝቱ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት መሆኗን ማሳያ በመሆኑ፤ ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግም በቱሪዝም ሚኒስቴር የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሊንሳ መኮንን ተናግረዋል።
 
ይህ የጥናት ውጤትና የሳይንስ ግኝት በመስኩ የመጀመሪያው የሳይንስ ግኝት በመሆን በ"ኔቸር" የጥናት መፅሔት እ.ኤ.አ መጋቢት 20 ቀን 2024 ለህትመት በቅቷል።
 
በመሐሪ ዓለሙ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top