“ግድቡ የኔ ነው” የሚለው አባባል በኢትዮጵያውያን ላይ ትልቅ የባለቤትነትና የተነሳሽነት ስሜት ፈጥሯል - አምባሳደር ስለሺ በቀለ

1 Mon Ago
“ግድቡ የኔ ነው” የሚለው አባባል በኢትዮጵያውያን ላይ ትልቅ የባለቤትነትና የተነሳሽነት ስሜት ፈጥሯል - አምባሳደር ስለሺ በቀለ

“ግድቡ የኔ ነው ወይም #ItsMyDam የሚለው አባባል ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ትልቅ የባለቤትነትና የተነሳሽነት ስሜትን እንዲፈጥርባቸው ማድረጉን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የሕዳሴ ግድቡ ዋና ተደራዳሪ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

በሕብረት በመሆን ከባድ ፈተናዎችን ጭምር እያለፉ የግድቡን ግንባታ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ያደረሱ አካላት በሙሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

እ.አ.አ በጥር ወር 2020 በአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አጠቃላይ ስራን የተመለከተ የሶስትዮሽ ድርድር ተካሄዶ ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ በወቅቱ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ላይ ሳሉ የተፈጠረውን መቼም እንደማይረሱት ይናገራሉ።

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከመካከለኛው መስራቅ የመጣች ጋዜጠኛ "ግድቡ ሲጠናቀቅ ማን ያስተዳድረዋል?" የሚል ተገቢነት የሌለው ጥያቄ ማንሳቷን ገልጸዋል።

በምላሹ It’s My Dam ወይም ግድቡ የኔ ነው በማለት እኛ ኢትዮጵያውያን እናስተዳድረዋለን የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ ግድቡ የኔ ነው ወይም #ItsMyDam የሚለው አባባል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ቀርቷል ነው ያሉት አምባሳደሩ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የሕዳሴ ግድቡ ዋና ተደራዳሪ ሆነው የሚያገለግሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አባባሉ በኢትዮጵያውያን ላይ ትልቅ የተነሳሽነትና የባለቤትነት ስሜት መፍጠሩንና ለግድቡ ለሚደረገው ድጋፍ ሕዝብን ለማስተባበር ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

“ለኢትዮጵያውያን የመተባበሪያ፣ የግንኙነትና የጋራ ልማት መልስ እንዲሆን ሊታወስ የሚችል ስንኝ ሆኗል'' ሲሉም ገልጸዋል።

በመስሪያ ቤቶች፣ በመኪናዎች ላይ በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት መሰራጨቱንና ይህም በሕዝቡ ላይ የተነሳሽነት ስሜት እንዲኖር ማድረጉን አመልክተዋል።

ግድቡ የኔ ነው ከሚለው አባባል ባሻገር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የቀሩና ትልቅ አበርክቶ ያላቸው አገላለጾች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ለአብነትም እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን፣ ሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ አድዋ ነው የሚሉትን አባባሎች በማንሳት በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ውስጥ እነዚህ አባባሎች በህዝብ ዘንድ ትልቅ መነሳሳት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 13 ዓመታት ሊሞላው ቀናት የቀሩት ሲሆን 13ኛ ዓመቱ “በሕብረት ችለናል” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል።

“በሕብረት ችለናል” ኢትዮጵያውያን በሕብረት በመሆን የግድቡን ግንባታ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ማድረሳቸውን ያሳያል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ታላቅ ስራ መስራት እንደሚችሉ የሚያንጸባርቅ መሪ ሀሳብ መሆኑንም ነው አምባሳደር ስለሺ የገለጹት።

መሪ ሀሳቡ ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን በማመስገን በቀጣይም ይህን አጋርነታቸውን እስከ ግድቡ ግንባታ ፍጻሜ ድረስ እንዲቀጥሉ ጥሪ እንደሚቀርብበት ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top