ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያን ጎበኙ

1 Mon Ago
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያን ጎበኙ

በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከቦርዱ አባላት ጋር በመሆን በኩባንያው የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ጉብኝት አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቦርድ አባላቱ ጉብኝታቸውን በአድዋ የድል መታሰቢያ በሚገኘው የኩባንያው ኤክስፒሪየንስ ማዕከል በመጀመር በፕሪሚየም አገልግሎት ማዕከል፣ ሞጁላር ዳታ ሴንተር እና የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ኩባንያው የኮኔክቲቪቲ ተደራሽነት እና ጥራት ከማሻሻል ባሻገር የዲጂታል ሶሉሽኖችን እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ የህዝብን ህይወት ለማቅለል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቴሌኮም እና በዲጂታል መሠረተ ልማት አቅም የተፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም የመንግስት ተቋማት አሰራሮቻቸውን በዲጂታል በማዘመን ፈጣን፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ የተገነቡ የዲጂታል አቅሞችን እንዲያውቁት እና እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ዕውን ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት እና አስተዋጽኦ በማድነቅ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቦርዱ ተገቢውን ድጋፍ እና አመራር እንደሚሰጥ መገለፁን ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top