“የኃይማኖት ተቋማት ተልዕኳቸው ድንበር የለሽ ነው” - ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

14 Days Ago
“የኃይማኖት ተቋማት ተልዕኳቸው ድንበር የለሽ ነው” - ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

ሁለተኛው አለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ “የእምነት ተቋማት ትብብር ለሰላም፣ ለሰብዓዊ ክብር፣ ልማትን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር እንዲሁም የጥላቻ ንግግርን፣ ግጭትን እና ብሄርተኝነትን ለመቃወም” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የኃይማኖት ተቋማት ተልዕኳቸው ድንበር የለሽ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው በየካቲት ወር መጀመርያ ታስቦ የሚውለውን ዓለምአቀፋን የወርቃማ ህግ ቀንን ታሳቢ በማድረግ የአለም የሀይማኖት ተቋማትን ትብብር ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀይማኖት ተቋማት ድኝበር የለሽ መሆናቸውን ያነሱት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በጉባኤው ጠቃሚና ተጨባጭ ልምዶች እና ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ኢ-ፍታዊነትን የምንቃወምበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሁሉንም የሰው ልጆች እንደ አንድ ቤተሰብ በማስተሳስር ኢ-ፍትሃዊነትን፣ በደልን እና ኢ-ሰብዓዊነትን መቆጣጠር አንዱ የጉባኤው አላማ እንደሆነም ነው የገለፁት፡፡

የመጀመሪያው ጉባኤ ሀገራዊ እና አለም አቀፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን በተለይ በዘላቂ ሰላም፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በእምነት ነፃነት ላይ ያተኮረ እንደነበርም ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስታውሰዋል፡፡

በቀደመው ጉባኤ እንደ እቅድ ተይዘው ከነበሩት ነጥቦች አንዱ የሆነውን ህብረቱን የቡድን 20 ቋሚ አባል ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ በብዙ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶች እና እምነቶች ብዝሃነትና በምድረ ቀደምት የተገነባች የሚለውን የቱሪዝም መገለጫ በተጨባጭ ለማሳየት የላቀ አስተዋፆ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል፡፡

በጉባዔው የሃይማኖት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

በአፎሚያ ክበበው እና ናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top