ለፍጹምነት የተጠጋው ፒኤስጂ ከማድሪድ

9 Hrs Ago 74
ለፍጹምነት የተጠጋው ፒኤስጂ ከማድሪድ
 
የሁለቱ ስፔናውያን እና የሁለቱ ፈረንሳውያን የከባድ ሚዛን ፍልሚያ ነው፡፡ ከፍጻሜ በፊት የሚደርግ ፍጻሜ::
 
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ፈረንሳዊው ገጣሚ አልፍሬድ ደሙሴት የክፍለ ዘመኑ ልጅ (child of the century) በተባለው መጽሀፉ ፍጹምነት የማይታሰብ ነው ቢልም ፒኤስጂ ግን ፍጹም ለመሆን ተቃርቧል፡፡
 
ከስፔናዊው አሰልጣኝ ሊዩስ ኤነሪኬ በኋላ አስፈሪ ሆኖ የተገነባው ፒኤስጂ በውድድር አመቱ ማግኘት ከሚጠበቅበት 5 ዋንጫዎች 4ቱን አሳክቷል፡፡ የሚቀረው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰበት የክለቦች አለም ዋንጫ ብቻ ነው፡፡
 
የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ለፍጻሜ ለማለፍ ከስፔኑ ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድ የሚገናኝበት ጨዋታ ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡
 
የፈረንሳይ ሊግ ዋንን ክብር በ9 ነጥብ ርቆ ያሸነፈው እና ታላላቆቹን ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ አርሰናል እና በፍጻሜው ኢንተር ሚላንን አሸንፎ ለመጀመርያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነው ፒኤስጂ በክለቦች የዓለም ዋንጫም አስፈሪ መሆኑን እያሳየ ይገኛል::
 
በተለይ በሩብ ፍጻሜው ምንም እንኳን ባለቀ ሰዓትም ቢሆን ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ አጥቶ ባየር ሙኒክን ያሸነፈበት መንገድ ረጅም ርቀት እንደሚጓዝ ማሳያ ሆኗል፡፡
 
የማድሪድ አለቃ ሆኖ ሳንቲያጎ በርናባው የደረሰው ወጣቱ ስፔናዊው አሰልጣኝ ዣቢ ኦሎንሶ የመጀመርያ ዋንጫውን ለማሳካት እና የውድድር አመቱን በድል ለመጀመር ምሽት በሚትላይፍ ስቴዲየም የመጀመርያውን ከባድ ፈተና በድል ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል፡፡
 
በሌላ በኩል ኬይሊያን ምባፔ የቀድሞ ክለቡን ለመጀመርያ ጊዜ የሚገጥምበት ይሆናል፡፡ በ256 ግቦች የፒኤስጂ የምንጊዜም ከፍተኛው ግብ አስቆጣሪው ምባፔ በህመም የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ቢያልፉትም ለወሳኙ ጨዋታ በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል፡፡
 
በግሉም በቡድንም ከፔኤስጂ ጋር የተሳካ አመት ያሳለፈው ሌላኛው ፈረንሳዊ አጥቂ ኡስማን ዴምቤሌ ለማድሪድ ተከላካዮች ትልቁ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
 
በውድድር አመቱ 164 ግቦችን ያስቆጠረው የኡስማን ዴምቤሌ፣ ከኪቪቻ ካቫርስኬሊያ እና ዲዘር ዱዌ ጥምረት አስፈሪውን የፒኤስጂ የፊት መስመር ፈጥሯል፡፡
 
ሁለቱ ቡድኖች ለ13ኛ ጊዜ በሚገናኙበት ጨዋታ ከፒኤስጂ በኩል ዊሊያን ፓቾ እና ሉካስ ሄርናንዴዝ በቅጣት አይሰለፉም። ኢድዋርዶ ካማቪንጋ በጉዳት ዲን ሁጅሰን ደግሞ በቅጣት ለማድሪድ ግልጋሎት የማይሰጡ ተጫዋቾች ናቸው። የ15 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮኑ ማድሪድ ከወቅቱ የአውሮፓ ምርጡ ቡድን የሚደርገው ትንቅንቅ::
 
በአንተነህ ሲሳይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top